Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በክልሉ የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት ተመለከቱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት ጎበኙ፡፡

በጉብኝታቸውም ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የችግኝና የተከላ ቦታዎች ዝግጅት መጠናቀቁን ተመልክተዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰንበክልል ደረጃ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸው÷ ለአብነትም የማንጎ፣ የቡና፣ የአቡካዶ፣ የብርቱካን፣ የዘይቱንና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አቶ ባበክር ኸሊፋ÷ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 74 ሚሊየን ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው 40 ሚሊየን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው÷ በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን እና የመትከያ ስፍራዎች ቀድሞ ለማዘጋጀት የተደረገወን ጥረት አድንቀው÷ ባለፉት ጊዜያት የተተከሉ ችግኞች የመጽደቅ ሂደታቸውም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ የተመራ ልዑክ በካማሺ ወረዳ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተዘጋጁ ችግኞችን መጎብኘቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.