Fana: At a Speed of Life!

ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ ለሚፈለገው ጠንካራ ቀጠናዊ ትስስር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ ለሚፈለገው ጠንካራ ቀጠናዊ ትስስር ወሳኝ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ሃገራዊና ቀጠናዊ የትስስር ጥናት ማዕከል የተሰኘው ተቋም መስራችና የታሪክ ባለሙያ እንዲሁም የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ኢብራሂም ሙሉ ሸዋ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በርካታ አፍሪካውያን ከነጻነታቸው ማግስት ጀምሮ በሃሳብ ደረጃ ሲያራምዱት የቆየው ጠንካራ ማህበረ ኢኮኖሚን የመመስረቱ ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች መፈተኑን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁንም ቢሆን ቀጠናዊ ትስስርን እዉን ለማድረግ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ከሁሉም ሊቀድም የሚገባ ተግባር እንደሆነና ቀጠናዊ ትስስርን እውን ማድረግ ደግሞ ለፖለቲካዊ መረጋጋቱ ተጨማሪ ሃይል እንደሆነ ተናግረዋል።

የሶሺዮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው፥ በአንድነት አብረው ጠንካራ ግንኙነት የመሰረቱ ሃገራትን ተሞክሮ ለራስ በሚመች መልኩ መተግበር ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ቀጠናዊ ትስስርን የማሳደጉ ጉዳይ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ያለው ሚና መዘንጋት ካለው ሚና አንጻር ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አቶ ዋሲሁን በላይ ገልጸዋል፡፡

ባለሙያዎቹ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታም ሀገርን ጠንካራ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ የማድረጉ የውስጥ የቤት ስራ ግን አሁንም ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጠንካራ ሃገራዊ ተቋማት ግንባታ እና በተግባር የሚገለጥ ታላቅ ራዕይ ወሳኝነት ሊዘነጋ እንደማይገባ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡

በአወል አበራ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.