Fana: At a Speed of Life!

ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው-የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥንቃቄዎች ላይ ሰራተኞች እያሳዩት ያለው መዘናጋት ወረርሽኙ እንዲስፋፋ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ገለጸ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንደገለጹት፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም በሰራተኞች እንዲሁም አጠቃላይ በማህብረሰቡ ዘንድ መዘናጋት ይስተዋላል።

በመሆኑም የወረርሽኙ መስፋፋትና በቫይረሱ የሚያዙ ሰራተኞች እየተበራከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሚመለከት እንደ ሰራተኛው ጋር የመዘናጋት ሁኔታዎች ይታያሉ፤መዘናጋት በመኖሩ እንደ ሀገር የቫይረሱ ስርጭት አሁን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ” ብለዋል።

ከሰራተኞች ባሻገር ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል ከዚህ ቀደም ያደርጉ የነበሩት ጥንቃቄ አሁን ላይ ተቀዛቅዞ ይገኛልም ብለዋል።

በተለይ በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በካፌና ሬስቶራንቶች፣ በመዝናኛ ስፍራዎችና በሌሎችም አካባቢዎች የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገው ጥንቃቄ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም በስራ ቦታ በፋብሪካዎች ላይ የሚከናወኑ ስራዎች ለንክኪ የተጋለጡ በመሆናቸው በስራ አካባቢዎቻቸው የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በአግባቡ በመጠቀምና ርቀትን በመጠበቅ መስራት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል ክትባቶች እየተሰጡ ቢሆንም ጎን ለጎን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ ከ262 ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፤ ከ3 ሺክ 800 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.