Fana: At a Speed of Life!

ሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል ዜጎች የድርሻቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል መንግሥት ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ቡድኖችን አደብ ለማስገዛት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና የህግ የበላይነትን የማስከበር መንግሥታዊ ስምሪት ሆን ተብሎ በሚለቀቅ የተሳሳቱ መረጃዎች ሕዝቡ ሳይወዛገብ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል ዜጎች የድርሻቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ጠየቀ፡፡
የክልሉ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በሰውና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ የክልሉ መንግስት ማምሻውን መግለጫ አውጥቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን የተቃጣበትን ጦርነት እየመከተና በጦርነቱ ምክንያት ከደረሱበት ሁለንተናዊ ጉዳቶች ለማንሰራራት ዘርፈ ብዙ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
የአማራ ህዝብ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ቀዳሚ የጥቃት ዒላማ በመሆኑ ወራሪ ቡድኑ በክልሉ ህዝብ ላይ ያላደረሰው ሰብአዊ ቀውስ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አለ ተብሎ አይወሰድም። በዚህም ምክንያት የክልሉ መንግሥትም ሆነ መላው ሕዝብ መክፈል የማይገባውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል።
መሪው ፓርቲም ይህንን ነባራዊ ሁኔታ መነሻ ያደረገና መላውን የአማራ ሕዝብ ያሳተፈ ተጨባጭ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። በጦርነቱ የጉዳት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ከደረሰባቸው ስነ ልቡናዊ ጥቃት እንዲያገግሙ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን የወደሙ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት የአደጋ ጊዜ አመራር እያረጋገጠ ይገኛል።
ይህ ተግባር ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ ውጭ የሚሳካ እንዳልሆነ የክልሉ መንግሥት ጽኑ እምነት አለው።
ምንም እንኳን ከወራሪው ኃይል ጋር በከፊል ጦርነት ውስጥ መሆናችን የሚዘነጋ ባይሆንም ጎን ለጎን በሕዝቦች መካከል በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት የሚያስችሉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና አያሌ የምክክር መድረኮችን እያከናወነ መሆኑም ይታወቃል።
ይሁን እንጂ አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ውላጅ የሆኑ ተስፈኛ ጽንፈኞችና አሸባሪዎች በአማራ ክልል ሕዝብ እና በአጎራባች ክልል ሕዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠርና የክልሉን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት ለመንሳት በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ለማጫር ተንቀሳቅሰዋል፤ እየተንቀሳቀሱም ይገኛሉ።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጃዊ ወረዳ በምንዋሰንባቸው የቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን በላያ እና አካባቢው፤ በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በመልካ ጅሎና ሲናናጆ ቀበሌ እንዲሁም በማእከላዊ ጎንደር ዞን በአንድ አንድ አካባቢዎች በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል በአንድነትና በፍቅር ለሺ ዘመናት አብሮ በኖረው የአማራ ሕዝብ መካከል እንዲሁም ከኦሮሞ እና ከጉሙዝ ሕዝብ ጋር የግጭት ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በአማራ እና በሁለቱም ክልሎች ህዝብ ሆደ ሰፊነት እና በጀግኖች የጸጥታ አካላት ተሳትፎ የጥፋት እና የእልቂት ፍላጎታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፤ እንዲከሽፍም ተደርጓል።
ይህንን የጥፋት ሙከራ ለመቆጣጠርና ለመቅረፍ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ይህ የጨነገፈ የጥፋት ተልእኮ ሙከራ ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ኃይሎች ምን ያህል በተቀናጀና ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ የአማራ ክልልን የግጭት ማእከል ለማድረግ አልመው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ በተጨባጭ ያረጋግጣል።
ስለሆነም መላው የአማራ ክልል ሕዝብ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሕዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር በህቡዕም ሆነ በገሃድ የሚንቀሳቀሱ የጽንፈኛ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ በመረዳት እንደወትሮው ሁሉ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ቡድኖችን አደብ ለማስገዛት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና የህግ የበላይነትን የማስከበር መንግሥታዊ ስምሪት ሆን ተብሎ በሚለቀቅ የተሳሳቱ መረጃዎች ሕዝቡ ሳይወዛገብ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመከላከል የዜግነት ድርሻችሁን እንድትወጡ የክልሉ መንግሥት በአክብሮት ይጠይቃል።
በሌላ በኩል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከጽንፈኛና ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ የጥፋት ትስስር በመፍጠር የአማራ ክልልን የቀውስ ሜዳ ለማድረግ፤ የክልሉን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት ለመንሳት እንዳሁም የህዝባችንን ሰላምና የመልማት እድል በመንፈግ ከድህነት እንዳይወጣ ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀን የጠላት እቅድ በመፈጸምም ሆነ በማስፈጸም እኩይ ተግባር ውስጥ የተዘፈቃችሁ አካላት ከድርጊታችሁ እንድትታቀቡ የክልሉ መንግሥት በጥብቅ ያሳስባል።
ከየትኛውም ጠላት ጋር የምናደርገውን ትግል ከሰላም ወዳድ ወገኖቻችን ጋር በመተባበር አጠናክረን የምንቀጥል ሲሆን እዚህ እና እዚያ በመርገጥ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል በግልፅም ሆነ በህቡዕ የምትንቀሳቀሱ ኃይሎች ከዚህ እኩይ ድርጊታችሁ የማትታቀቡ ከሆነ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ማንኛውንም አይነት ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አበክሮ ያስጠነቅቃል።
በመጨረሻም የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉን ልማትና የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል በሚወስደው ማንኛውም አይነት ህጋዊ እርምጃ መላው የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም በድጋሚ የአክብሮት ጥሪውን ያሳተላልፋል።
በሕዝብ ስም እየነገዱ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ቅርቃር ውስጥ ማስገባት የሕዝብ ፀርነት እንጂ ሕዝባዊነት አይደለም!
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.