Fana: At a Speed of Life!

ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችንና የሉዓላዊነታችን ተምሳሌት በመሆኑ ልናከብረው ይገባል – ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችን፤ የሉዓላዊነታችንና የነፃነታችን ምልክትና ተምሳሌት በመሆኑ ከፍ ባለ ደረጃ ልናከብረው ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

14ኛው የሰንደቅ ዓለማ ቀን “በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉአላዊነት ለሰንደቅ ዓላማ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል አዲስ አበባን ጭምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከበረ ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ክብረ በዓል ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመዲናዋ በተካሄደው በዓል ፥ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣የአዲስ አበባ ከተማ አፈጉ ባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ተገኝተዋል።

በዓሉ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የተከበረ ሲሆን ÷የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ፣የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መለው ኢብራሒም የክልሉ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ሐላፊ አቶ መሀመድ ሻሌ፣ የሐገር መከላከያ ሰራዊት ፣የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሐገር ሽማግሌዎችና የመንግስት የስራ ሐላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።

አቶ ሙስጠፌ የባንዲራ ቀን የተሰየመው ሁሌም የምናከብረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የአንድነት አርማ ሆኖ በህብረት ጥላ ስር የማምጣት ተልዕኮ አለው ብለዋል።

በተመሳሳይ የሰንደቅ አላማ ቀን በሃረሪ ክልል የተከበረ ሲሆን÷ በዓሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አዲስ አለም በዛብህ ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡

እንዲሁም 14ተኛው የሰንደቅ ዓለማ ቀን በሲዳማና በኦሮሚያ ክልል ተከብሯል፡፡

በመረሐ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሶ ጨምሮ ሌሎች ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን÷ አቶ ደሰታ ሌዳሞ ባንዲራ አባቶቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለው ያመጡ በመሆኑ ሁላችንም ለባንዲራ ክብር መስጠት ይገባናል ነዉ ያሉት፡፡

እንዲሁም በዓሉ በደቡብ ክልል ሃዋሳ የተከበረ ሲሆን ÷በበዓሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ፣የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰንደቅ አላማችን የብሄራዊ አንድነትና የሀገር ፍቅርና ስሜት መገለጫ ነው ብለዋል።

እንዲሁም 14ተኛው የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በአፋር ክልል ሰመራ ተከብሯል፡፡

የአፋር ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ – ጉባዔ ወ/ሮ አስያ ከማልና በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አሰተዳደር ክላሰተር አሰተባባሪ አቶ አህመድ መሀመድ ሰንደቅ አላማ በመስቀል የበዓሉን ስነ ስርአት አካሂደዋል ።

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የቤንሻንጉል ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዱላዚም መሃመድ በተገኙበት በክልሉ አሶሳ ከተማ የሰንደቅ አላማ በመስቀል ስነ-ስርዓት ተከብሯል፡፡

በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል የባንዲራ ቀንን ያከበረ ሲሆን÷ የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፣ ዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና የስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀበረቅበት የአንድነትና ህብረት አርማና ምልክት ነው ብለዋል።

ዕለቱ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጨምሮ በተለያዪ መስሪያ ቤቶችም ተከብሯል።

በዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ በዓል፥ ኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞዋን በአዲስ ምዕራፍ ለመጀመር አዲስ መንግስት በመሰረተችበት ማግስት የተካሄደ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለየት ባለ መልኩ የተከበረ መሆኑን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.