Fana: At a Speed of Life!

ሰዎችን በማገት 30 ሚሊየን ብር ሲጠይቁ እና ከባድ ውንብድና ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ 5 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮማንደርና ደህንነት ነን እያሉ ሰዎችን በማገት 30 ሚሊየን ብር ሲጠይቁ እና ከባድ ውንብድና ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ 5 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ዛሬ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የታዩት ተጠርጣሪዎች ያሬድ ኦሊቃ እና ፍቃዱ እዮኤልን ጨምሮ አምስት ናቸው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አባባ ከተማ ለከባድ ውንብድና ወንጀል ተደራጅተው ሰዎችን ሲያግቱ እንደነበር በማስረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በተለይም ህዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሙሴ ክብረአብ የተባለ ግለሰብን አግተው ወደቤተሰቦቹ ስልክ በመደወል 30 ሚሊየን ብር ካላመጣችሁ በህይወት አታገኙትም እያሉ ሲያሰፈራሩ እንደነበር ባደረኩት ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ።

ተጠርጣሪዎቹ ሌሎች ሲፈጽሟቸው የነበሩ የወንጀል ድርጊቶች መኖራቸውንና ምርመራው እንዳይደናቀፍ በማሰብ በችሎት አለመግለጹን በመጥቀስም በምርመራ ያገኘኋአው ማስረጃዎች አሉኝ ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ እየደወሉ ብር ሲጠይቁበት የነበረውን የስልክ ልውውጥ ለሚመለከተው አካል ልኮ የቴክኒክ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም አስረድቷል፡፡

በወቅቱ አግተውት የነበረው ግለሰብ ጉዳት ያደረሱበት መሆኑን ተከትሎ የህክምና ማስረጃ መጠየቁንም ተናግሯል።

እያከናወንኩ ካለው ሰፊ ምርመራ አንጻር ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲልም መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ ፍርድ ቤቱ በዋስ እንዲለቃቸው ጠይቀዋል።

5ኛ ተጠርጣሪ ከ2ኛ ተጠርጣሪ ጋር ዝምድና እና ወዳጅነት አለን በመኖሪያ ቤቴ የተገኙት የባንክ ደብተሮች የማውቃቸው ሰዎች የባንክ ደብተሮች ናቸው፤ ገንዘብ አልተቀበልኩም ሲል ተከራክሯል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው ከያሬድ ኦሊቃ ጋር በመሆን የታጋቹ ሙሴ ክብረአብን ቤተሰብ 30 ሚሊየን ብር አምጡ እያለ ሲደውል እንደነበር በማስረጃ አረጋግጫለሁ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ጉዳዩን የተከታተለው ቸሎቱም ቢወጡ ማስረጃ ሊያጠፉ ይችላሉ ሲል ለተጨማሪ ምርመራ 7 ቀናትን ለፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.