Fana: At a Speed of Life!

ሱዳን በሶስተኛ ወገን የተደገሰላትን የጦርነት ወጥመድ  በመተው ችግሩን በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን አለባት-ጀነራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)  ሱዳን በሶስተኛ ወገን የተደገሰላትን የጦርነት ወጥመድ ወደ ጎን በመተው የድንበሩን ጉዳይ በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባት የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የትግራይ ህዝብ ጁንታው ተመልሶ እንደሚመጣ አስመስለው ባዶ ህልም በሚነዙ አካላት ሳይደናገር ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እያደረገ ያለውን ደጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት።

ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ይህን ያሉት ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።

ኢትዮጵያና ሱዳን የሚገጥማቸው የውስጥ ችግር ያልበገረው ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳለቸው አስታውሰዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ሱዳን የገጠማት ፖለቲካዊ ችግር ሱዳናዊያንን ሳይጎዳ በሰላም እልባት እንዲያገኝ በማድረግ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።

ነገር ግን  የኢፌዴሪ መንግስት በጽንፈኛው የህወሃት ጁንታ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ መግባት ጠቁመዋል።

ይህም አገራቱ ካለቸው ወዳጅነት አንጻር ከሱዳን የማይጠበቅ  አሳዛኝ ተግባር ነው ብለዋል።

የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ ከመግባቱ ጀርባ የግድቡን ድርድርና ግንባታ ማስተጓጎልን ያለመ ሶስተኛ አካል መኖሩን ጠቅሰዋል።

ይህ አካል ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር እርምጃ ላይ መሆኗንና ሱዳን ደግሞ ፖለቲካዊ ሽግግር ላይ መገኘቷን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀሙንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮች አዲስ አለመሆናቸውንና በሰላም ሲፈቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት ጀነራል ብርሃኑ፤ የአሁኑ ግን የሶስተኛ ወገን እጅ ስላለበት ችግሩ ጎላ ብሎ ወጥቷል ብለዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላም መፍታት እንጂ ከወዳጅ ሀገር ሱዳን ጋር ወደ ጦርነት መግባት እንደማትፈልግም ገልጸዋል።

ሱዳንም በሶስተኛ ወገን ከተደገሰላት የጦርነት ወጥመድ ወጥታ ችግሩን በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባትም ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡም ጉዳዩን በሚመለከት በሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ተቋሞች ደረጃ ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟል ብለዋል ጀነራል ብርሃኑ ጁላ።

በተያያዘ ዜና በመተከል የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ሽፍታ እንቅስቃሴ ከግምት ወስጥ ባስገባ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

ሽፍታው ካለው ባህሪ አንጻር እንቅስቃሴው የሚገታው የጸጥታ ተቋማት ከሚወስዱት እርምጃ በተጓዳኝ ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅርና የህዝብ አደረጃጃት በመፍጠር መሆኑንም ነው ያነሱት።

በዞኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ መንግስታዊ አደረጃጃትና ማህበረሰቡም አካባቢውን እንዲጠበቅ የሚያደርግ አሰራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

እስካሁን በተወሰደው እርምጃም በርካታ የህገ ወጥ ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንም ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የተደበቁ ቀሪ ተፈላጊ የጁንታው አባላትን ከማደን ተግባር ጎን ለጎን ክልሉን መልሶ በማደራጀት ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፌደራል ጸጥታ ተቋማት የተወጣጡ አንድ ሺህ የሚሆኑ አባለት ያለው መንግስት በክልሉ እያደረገ ያለው ሰብአዊ ድጋፍ እስከ ቀበሌ እንዲዳረስ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህ ባለበት ሁኔታ ጁንታው ተመልሶ እንደሚመጣ አስመስለው ባዶ ህልም በመንዛት ህዝብን ለማደናገር የሚሞክሩ አካላት እንዳሉም አንስተዋል።

ጁንታው በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛው ወታደራዊ አደረጃጃት እንኳ እንዳይኖረው ተደርጎ በመደምሰሱ ምክንያት እንኳንስ ሊደራጅ ቀርቶ አመራሮቹ በየገደሉ ተበታትነው እየተያዙ ይገኛሉ ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት በህወሃት ጁንታ ስር ተጎሳቅሎ ኖሯል፤ ይህን የስቃይ ዘመን ተመልሶ እንዲመጣበትም አይፈልግም ነው ያሉት ጀነራል ብርሃኑ።

የትግራይ ህዝብ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን በማገዝ ረገድ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.