Fana: At a Speed of Life!

ሳዑዲ አረቢያ የኡምራ ጸሎት ከመስከረም 24 ጀምሮ እንዲካሄድ ወሰነች

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳዑዲ አረቢያ በአገሯ ውስጥ ለሚገኙ ምዕመናን የኡምራ ጸሎትን ከመስከረም 24 ጀምሮ እንዲያካሂዱ መፍቀዷን አስታወቀች፡፡

ሳዑዲ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለሰባት ወራት እገዳ ጥላ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አሁን ይፋ በሆነው ውሳኔ በየዕለቱ 6 ሺህ ዜጎች የጸሎት ስነስርዓት እንዲያካሂዱ መወሰኑ ነው የተሰማው፡፡

ይህ ቁጥር ከጥቅምት 8 ጀምሮ አሁን ካለበት ወደ 75 በመቶ እንደሚያድግ ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሳዑዲ ከጥቅምት 22 ጀምሮ ከተወሰኑ አገራት የሐጅና ኡምራ ተጓዦችን እንደምታስተናግድ አስታውቃለች፡፡

ኮሮና ቫይረስ እስከሚያበቃ ድረስም ይህ አሰራር እንደሚቀጥል የሳዑዲ ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡

የሃጅና ኡምራ ጉዳዮች ሚኒስትር ምዕመናኑን የሚመዘግብበት የሞባይል መተግበሪያ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

በዚህም ተመዝጋቢዎች በመተግበሪያው ላይ የሰፈሩ የጤና መመሪያዎችን መከተል እንደሚገባቸው ነው የተነሳው፡፡

የሳዑዲ መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሐምሌ ወር በተካሄደው የጸሎት ስነስርዓት ላይ 10 ሺህ ምዕመናን መካፈላቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

ይህም በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ ቁጥሩ እጅግ አነስተኛ የሆነ ምዕመናን የተሳተፉበት ነበር ተብሏል፡፡

ሳዑዲ በሃጅና ኡምራ በየዓመቱ ወደ 12 ቢሊየን ዶላር እንደምታገኝ ይፋዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሳዑዲ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ ከተያዙ 330 ሺህ ሰዎች 312 ሺህ የሚሆኑት ሲያገግሙ 4 ሺህ 500ዎቹ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አገሪቱ በኮቪድ ምክንያት ለስድስት ወራት ጥላ የቆየችውን የዓለም አቀፍ በረራ እገዳ በከፊል ማንሳቷ የሚታወስ ነው፡፡

ምንጭ፡-አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.