Fana: At a Speed of Life!

ስካይ ላይት ሆቴል ባለ 5 ኮከብ ደረጃ አገኘ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስካይ ላይትን ጨምሮ የአራት ሆቴሎችን የኮከብ ደረጃ ይፋ አድርጓል።

በዚህ መሰረት ስካይ ላይት ሆቴል ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ሲያገኝ፥ ዴንቨር እና በላይ ኢንተርናሽናል ሆቴል የባለ 2 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቤርኖት ሆቴል ባለ 1 ኮከብ ደረጃ ተሰጥቶታል።

የሆቴሎች ግምገማ እና ደረጃ አሰጣጡ ሙሉ በሙሉ በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑም በዚህ ወቅት ተገልጿል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳሁን በ2011 ዓ.ም ለ87 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ መሰጠቱን አስታውሰዋል።

የኮከብ ደረጃው በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን፥ ከደረጃ አሰጣጡ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ቅሬታ አለመቅረቡን አንስተዋል።

አያይዘውም ቀደም ባሉት አመታት በውጭ ባለሙያዎች ይከናወን ከነበረው የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ይነሳ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ይህን ችግር መቅረፍ በሚያስችል መልኩ የሃገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፥ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የእውቀት ሽግግር ማድረግ የሚችሉበት አቅም መፈጠሩን አስረድተዋል።

ባለ 5 ኮከብ ደረጃ ያገኘው ስካይ ላይት ሆቴል በቀጣይ ያገኘውን ደረጃ በሚመጥን መልኩ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጾ፥ በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ሎጅዎችን ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

በዘቢብ ተክላይ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.