Fana: At a Speed of Life!

ስድስቱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አዲሱን የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ለመቀላቀል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዞቹን አርሰናል ፣ ቼልሲ፣ ማንቼስተር ዩናይትድ ፣ ማንቼስተር ሲቲ ፣ ቶተንሃም፣ ሊቨርፑል  እንዲሁም ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ኤሲ ሚላን ፣ ጁቬንቱስ እና ኢንተር ሚላን የሚሳተፉበትን ሱፐር ሊግ ለመቀላቀል ስምምነት ላይ ደረሱ።

ይህ የአውሮፓን ቻምፒዮንስ ሊግን ለመተካት ያስችላል የተባለው ውድድር በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ውድቅ ተደርጓል።

ሱፐር ሊግ በሚል ስያሜ የተመሰረተው ውድድር የተጠቀሱትን 12 ክለቦች እና ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሱ ሶስት ክለቦችን በቋሚነት በመያዝ ለማካሄድ ያለመ ነው።

በውድድሩ ከእነዚህ 15 ቋሚ ቡድኖች ባሻገር ሌሎች 5 ክለቦች በየውድድር ዘመኑ በሊጎቻቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።

የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ክለቦቹ በየሳምነቱ አጋማሽ  ውድድር ለማካሄድ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፥  ሱፐር ሊጉ ከየሊጎቻቸው ውድድር ጎን ለጎን የሚካሄድ ነው ብሏል።

የመጀመሪያው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ፕሬዚዳንት የሪያል ማድሪዱ ፕሬዚዳንት ፍሎሬቲኖ ፔሬዝ አዲሱ ውድድር ሁሉንም የእግር ኳስ ደረጃዎች ያግዛል ብለዋል።

ነገር ግን ፊፋ እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ቡድኖች እና ተጫዋቾች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ይህም በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ተጫዋቾች የሀገራቸውን ብሄራዊ ቡድን እንዳይወክሉ እስከማድረግ የሚደርስ መሆኑም ነው የተነገረው።

ውድድሩን የአሜሪካው ጂፒ ሞርጋን በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ስፖንሰር ለማድረግ የተስማማ ሲሆን ለክለቦቹ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በተሻለ ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑ ተነግሯል።

በርካታ እግር ኳስ አፍቃሪ ቤተሰቦች ግን “ይህ ውድድር አግላይና እግር ኳስን የሃብታምና የደሃ የሚያደርግ ነው” በሚል ቁጣቸውን እያሰሙ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.