Fana: At a Speed of Life!

ስድስት ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ ተከሳሾች በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ ጃንቹታ ቀበሌ ስድስት ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደሉ አራት ተከሳሾች በዕድሜ ልክ እና የ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
አንደኛ ተከሳሽ ካባ ሙሉጌታ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ማንታል ጉሉ፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ማስረሻ አለማየሁ እና አራተኛ ተከሳሽ ኤልያስ ታጳ የእስራት ቅጣቱ የተወሰነባቸው፥ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት እስከ 9፡00 ሰዓት ባለ ጊዜ ውስጥ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ በጃንቹታ ቀበሌ በስድስት ሰዎች ላይ ግድያና የዘረፋ ወንጀል በመፈፀማቸው ነው ።
የደቡብ ቤንች ወረዳ ፖሊስ፥ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ከዞኑ ፖሊስ ጋር ባደረገው ምርመራ በነበረው የመዋቅር ጥያቄ ለመንግስት መረጃ ሰጥታችኋል በሚል ግድያ በመፈፀም፣ ንብረታቸውን በማቃጠል እንዲሁም የዘረፋ ወንጀል መፈፀማቸውን በምርመራ አረጋግጧል።
የዞኑ ዐቃቤ ሕግ÷ ተከሳሾች ከገደሏቸው ስድስት ሰዎች መካከል ሦስቱን መኖሪያ ቤት ውስጥ እንዳሉ በእሳት ማቃጠላቸው በሰውና ሰነድ ማስረጃ ተመስክሮባቸው መከላከያ ባለማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ. ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት፥ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 117(1) መሠረት ሁለተኛ ተከሳሽ ማንታል ጉሉ እና ሦስተኛ ተከሳሽ ማስረሻ ዓለማየሁ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ካባ ሙሉጌታ እና አራተኛ ተከሳሽ ኤልያስ ታጳ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ያልፈጸሙ በመሆናቸው÷ እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ መተላለፉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.