Fana: At a Speed of Life!

ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊው የኮቪድ 19 መከላከያ ጥንቃቄ በማድረግ እንደሚጀመሩ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ አስፈላጊው የኮቪድ 19 መከላከያ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
በትናንትናው ዕለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ስፖርታዊ እንቅስቀሴ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ መወሰኑን ተከትሎ የኢፊድሪ ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ክቡር አቶ ዱቤ ጅሎ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል ፡፡
በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሲባል ስፖርታዊ ስልጠናዎች፣ ውድድሮች በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ መደረጉ ይታወቃል ፡፡
የኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መፈቀዳቸውን አስመለክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን በአዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ለሚመለከተው አካል ፍቃድ እንዲሰጥ መቅረቡን ገልጸዋል።
በዚህም ፕሮቶኮሉን መነሻ በማድረግ እና የጤና ሚኒስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ተወስኗል ብለዋል ፡፡
ነገር ግን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ አስፈላጊው የኮቪድ -19 መከላከያ መንገዶች እና ጥንቃቄዎች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
በተለይም ስልጠናዎች እና ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት ከማዘውተሪያ ዝግጅት ፣ የሰው ሀይል ቁጥር እና ሌሎች አስፈላጊ የመከላከያ ግብዓቶች መሟላታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት ስፖርቱን ሲያስጀምሩ በኮሚሽኑ እና በጤና ሚኒስቴር የወጣውን መመሪያ በየደረጃው ስራ ላይ እንዲውል ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው መጠቆማቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ይህን የሚከታተልም የብሔራዊ ኮሚቴ ፣የጤና እና የፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል ብለዋል ፡፡
በተዋረድም በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችም ኮሚቴዎች ተቋቁመው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ፡፡
መመሪያውን ተላልፎ የሚገኝ አካል ላይም አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል ፡፡
ከዚህ ባሻገር ኮሚሽኑ ስፖርቱን በአሠራር እና በአደረጃጀት ለማስተካከል እና ውጤታማ ለማድረግ ሀገር አቀፍ የስፖርት ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰራ በመግለጫቸው አንስተዋል ፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.