Fana: At a Speed of Life!

ሶስቱ ሀገራት በሰባት ቀናት የሶስትዮሽ ድርድሩን በማካሄድ በቀጣይ አካሄዶች እና የጊዜ ሰሌዳ ስምምነት ላይ ለመድረስ መግባባታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሰባት ቀናት ውስጥ የሶስትዮሽ ድርድሩን በማካሄድ በቀጣይ የድርድሩን አካሄዶች እና የጊዜ ሰሌዳ ስምምነት ላይ ለመድረስ መግባባታቸው ተገለጸ፡፡

ሀገራቱ በሰባት ቀናት ውስጥ ድርድሩን በማካሄድ በቀጣይ የድርድሩ አካሄዶች እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነት መድረስ፣ ልዩነት ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነትን ለማጥበብ እና ውጤቱንም ለውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀጣይ ስብሰባ ለማቅረብ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ቀደም ብሎ በጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሃገራቱ በጻፉት ደብዳቤ እና ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም በበይነ-መረብ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር እየተካሄደ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የተመለከተው የሶስትዮሽ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቀደም ብሎ በጥቅምት መጀመሪያ ከኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች ጋር በስልክ ባደረጓቸው ውይይቶች በተደረሰው መግባባት እና ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ድርድሩን ለመቀጠል ስምምነት ላይ መደረሱም ነው የተገለጸው።

የመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባም በሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትር ሰብሳቢነት ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.