Fana: At a Speed of Life!

ሶዶ ከተማ በመርካቶ የገበያ ማዕከል በእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የ40 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን በወላይታ ሶዶ ከተማ በመርካቶ የገበያ ማዕከል በደረሰው የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከ40 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

በዚህ የእሳት አደጋ 47 ሺህ 251 የሚሆኑ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተጎዱ ሲሆን 1 ቢሊየን 57 ሚሊየን 670 ሺህ ብር የሚያወጣ ሃብት መውደሙም ተገልጿል።

በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና መልሶ የማቋቋም ስራ በተለያዩ አካላት እየተከናወነ ሲሆን ውድመቱ ከፍተኛ በመሆኑ ከፌደራል ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በሁለቱ ተቋማት የተደረገውን ድጋፍ ለወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ አስረክበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት የደረሰውን ጉዳት በመጎብኘት ተጎጂዎችን ማጽናናት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ገቢ ከመሰብሰብ በተጓዳኝ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ተጎጂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ አብይ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በህገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኮንትሮ ባንድ ቁሳቁሶችን በተለያየ መንገድ ተጎጂ ለሆኑ አካላት ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለተጎጂዎች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በኮንትሮባንድና ህገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሀብቶችን በመያዝ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ የተጋለጡ ወገኖችን የመደገፍ ተግባር እንዳለ የገለፁት ኮሚሽነሩ በወላይታ ሶዶ መርካቶ ገበያ ማዕከል እሳት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከዚሁ ሀብት ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።

የምግብ ዘይት 6 ሺህ 800 ሊትር፣ ስኳር 10 ሺህ ኪሎ ግራም፣ የተለያዩ አልባሳት 30 ሺህ ኪሎ ግራም፣ 169 የተለያዩ ብርድልብሶች፣  5 ሺህ ጫማዎች እና 993 ቆርቆሮ በአጠቃላይ 40 ሚሊየን 79 ሺህ 600 ብር የሚገመቱ የተለያዩ ቁሳቁሶች በድጋፉ ተካተዋል።

እነዚህ ድጋፎች በቀጥታና በፍትሃዊነት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዲደርስ አደራ ተብሏል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ የፌደራል መንግስት ተቋማት የሚያሳዩት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው በልዩነት የገቢዎች ሚኒስቴርና በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት በየጊዜው ለሚያደርጉት ፈጣንና ወቅታዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳደር ዶክተር እንድሪያስ ጌታ ድጋፉን በፍትሃዊነት ለማዳረስ ኃላፊነት መውሰዳቸውን ጠቅሰው በአደጋው የደረሰው ውድመት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አውስተዋል።

በመለሰ ታደለ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.