Fana: At a Speed of Life!

ሻይ መጠጣት የልብ በሽታና የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ተጋላጭነትን ይቀንሳል – ጥናት

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሻይ መጠጣት የልብ በሽታና የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ አንድ ጥናት አመላከተ።

በጥናቱ መሰረት በሳምንት ውስጥ ከሶስት ጊዜ በላይ ሻይ መጠጣት የልብ ጤንነትን እንደሚያሻሽልና ረጅም እድሜ ለመኖር እንደሚያስችል ተገልጿል።

ለረጅም ጊዜ በቻይና ሜዲካል ሳይንስ አካዳሚ የተካሄደው ይህ ጥናት ከዚህ ቀደም የልብ፣ የጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ እና የካንሰር በሽታ ያልነበረባቸውን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን አሳትፏል፡፡

የጥናቱን ተሳታፊዎች በሳምንት ከሶስት ጊዜ በላይ ሻይ የሚጠጡ እና የማይጠጡ በሚል በሁለት ቡድን እንዲከፈሉ ተደርጓል።

ለ7 ዓመት በተካሄደ ክትትል በተደጋጋሚ ሻይ የሚጠጡ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ጤናማ ሆኖ የመቆየት እድል አላቸው ነው የተባለው፡፡

ሻይን መጠጣት ልምድ ያደረጉ ሰዎች ለልብ በሽታና ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ የመጋለጥ እድላቸው በ20 በመቶ፣ በበሽታው የመሞት እድላቸው ደግሞ በ22 በመቶ እንዲሁም በሌሎች በሽታዎች የመሞት እድላቸው በ15 በመቶ እንደሚቀንስ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የዚህ ጥናት አካል የሆነ ምርምር 14 ሺህ ሰዎችን በማሳተፍ ተካሂዷል፡፡

በሁለቱም ጥናቶች ሻይ የመጠጣት ልምድ ያላቸው ሰዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ የተገለፀ ሲሆን በድንገኛ የልብ በሽታ እና የጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ የመጋለጥ እድላቸው በ56 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል፡፡

ሆኖም ሌሎች ባለሙያዎች ባወጡት አስተያየት ይህ ጥናት የምልከታ ብቻ መሆኑን በመግለፅ ሻይ መጠጣት እና የልብ በሽታ እንዲሁም ረጅም እድሜ መኖር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ምንጭ፡- healthline.com/

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.