Fana: At a Speed of Life!

ቀጠናውን በአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን በጥበባት እና በባህል ፌስቲቫልም የሚታወቅ እናደርገዋለን-አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ቀጠናውን በአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን በጥበባት እና በባህል ፌስቲቫልም የሚታወቅ እናደርገዋለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ከሰኔ 7 እስከ 12 2014ዓ.ም የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል በአዲስ አበባ አዘጋጅቷል፡፡

ይህንንም  ቀጠናዊ ፌስቲቫል ለማሳካት ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን÷ የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል ለቀጠናችን ሰላም የህዝቦች ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የባህል ዲፕሎማሲን በትኩረት መከወን እንደሚገባ እና በውጭ ጉዳያችን በኩል ዋናው የምንረባረበት የትኩረት ማዕከላችን የጎረቤት ሀገራትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት መፍጠር መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚታወቀው በጦርነት፣ በድርቅ፣ በርሃብ እና በስደት ነው ያሉት አቶ ደመቀ ይህንን ገፅታ መቀየር የምንችለው ሕዝብና ሕዝብን በጥበባትና በባህል በማስተሳሰር ተፈጥሮ ያደለችንን ፀጋ ተጠቅመን ቀጠናውን ስናለማ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጥበብና የባህል ቋት መሆናቸውን እና የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫልን በጋራ ተርባርቦ በማቋቋም የማይቋረጥ የግንኙነት መሰረት መጣል ይቻላል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ቀጠናውንም በአትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን በጥበባት እና በባህል ፌስቲቫልም የሚታወቅ እናደርገዋለን ያሉት አቶ ደመቀ በቀጠናችን በጋራ መልማት እድገትን የጋራ ገበያን ማስፋፋት የቀጠናው ህዝቦች የህልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውንም ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ጎረቤት መር በሆነ ግንኙነት ለዘመናት የዘለቀውን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ግንኙነት በጥበብና በባህል በማስተሳሰር እና በማጎልበት በቀጣይ ቀጠናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳስርና የቀጠናውን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መስረት የሚጣልበት ፌስቲቫል ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

 

የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫልም የሙዚቃ፣ የፊልም፣ የስዕልና ቅርጻ ቅርጽ ፌስቲቫል፣ የመጻሕፍትና የዕደ ጥበባት ዐውደ ርዕይ፣ የሲምፖዚየም እና የስፖርት ፌስቲቫሎችን በውስጡ የያዘ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያን ገፅታ በማስተዋወቅ፣ የቀጠናውን ሀገራት ሕዝቦች በማስተሳሰር፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንድንሆን ስለሚያደርገን አጋር አካላትና ባለድርሻ አካላት አብረን እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.