Fana: At a Speed of Life!

ቅዝቃዜን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውለውን የከሰል መርዛማ ጋዝ እንዴት መከላከል ይቻላል?

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቅዝቃዜን ለመከላከልና ለምግብ ማብሰያነት አገልግሎት ላይ የሚውለው ከሰል በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተያዘ ሕይወትን ከማሳጣት እስከ የዕድሜ ልክ ህመም እንደሚዳርግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቅዝቃዜን ለመከላከል በሚል ከሰልን ሲጠቀሙ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካላደረጉ÷ የከሰል ጭስ ሞትን ጨምሮ የዕድሜ ልክ ህመም ለሆኑት የአዕምሮ ጉዳትና የልብ በሽታ ያጋልጣል፡፡
በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት÷ የከሰል ጭስ በዓይን የማይታይና ሽታ አልባ መርዛማ ጋዝ አለው፡፡
ይህ ጋዝ የሚፈጠረውም ጋዝ፣ ዘይት፣ ከሰል ወይም እንጨት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው ባለማለቃቸው ነው፡፡
የከሰል ጭስ በአካባቢያችን በሚኖርበት ጊዜ አየር ወደ ውስጡ በሚሳብበት ጊዜ÷ በደም ውስጥ በመግባት የቀይ የደም ህዋስ አካል የሆነውና ኦክስጅን ተሸክሞ ለተያዩ የሰውነት ክፍሎች ከሚያደርሰው ሂሞግሎቢን ጋር በመቀላቀል ካርበ ኦክሲሄሞግሎቢን ይሆናል፡፡
ይህ ከሆነ በኋላ ደም ኦክስጅን መሸከሙን ያቆማል፤ በዚህ የተነሳ የህዋሶቹ አነስተኛ ክፍሎች ይጎዳሉ፤ ብሎም ይሞታሉ፡፡
በከሰል ጭስ ወይም በካርበን ሞኖክሳይድ የተጠቃ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች፥የራስ ምታት፣ ራስ ማዞርና መታመም፣ የድካም ስሜትና ግራ መጋባት፣ ሚዛንን ለመጠበቅ መቸገር፣ የዕይታና የትውስታ ማጣት፣ ራስን መሳት፣ በአንድ ነገር ላይ አትኩሮት ማጣት፣ የሆድ ሕመም እንዲሁም ለመተንፈስ መቸገር ምልክቶች ሊታዩበት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
የከሰል ጭስን እንዴት መከላከል ይቻላል፥በከሰል ምግብ ማብሰል ሲያስፈልግ በቂ አየር እንዲያገኝ (ከተቻለ ከቤት ውጭ) ከቤት ውጭ ማብሰል ካልተቻለ ደግሞ ሙሉ በመሉ ከተቀጣጠለና ጭሱ መጥፋቱ ሲረጋገጥ ወደ ቤት ማስገባት ይመከራል፡፡
በተጨማሪም የከሰል ምድጃ እየተጠቀሙ በር እና መስኮት አለመዝጋት፣ በከሰል ምግብ አብስለው ሲጨርሱ በውኃ ማጥፋትና በርና መስኮት በመክፈት ቤቱን ማናፈስ እንዲሁም ከሰል ቤት ውስጥ አለማቀጣጠልን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ከሰል ቤት ውስጥ አቀጣጥሎ ማሸለብ ወይም መተኛት አደጋው የከፋ በመሆኑ ከእነዚህ ድርጊቶች ይቆጠቡ።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.