Fana: At a Speed of Life!

ቅድሚያ ለሰላም ሰጥተን እንሰራለን-የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት3፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላምና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ከተማ ምንም ነውና ቅድሚያ ለሰላም ሰጥተን እንሰራለን ሲሉ አዲሱ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ተናገሩ።
የጎንደር ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 9ኛ አመት1ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው አቶ ዘውዱ ማለደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ከተማዋን እንዲመሩ በሙሉ ድምፅ ተመርጠው ተሹመዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በጎንደር ከተማ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ቃላ መሃላ ፈጽመዋል።
በወቅቱም ጎንደርን ለማገልገል እድሉን ሳገኝ እኔና በአዲስ የሚዋቀረው ካቢኔ የመጀመሪያ ስራችን የከተማችንን ህዝብ ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ እና የህዝቡን ሰዉ ሰራሽ የኑሮ ዉድነት ማስተካከል ቁልፍ ተግባራችን ይሆናል ብለዋል።
ሁሉም የህብረተሰባችን ክፍል በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባት ከተማ ማድረግ የማንደራደርበት ጉዳይ ነው ያሉት ተቀደዳሚ ከንቲባው፥ ደህንነትና የመኖር ዋስትና እንዳለው የማይሰማው ማህበረሰብ ውስጥ የኢኮኖሚና የዕድገት ፍላጎት ዘበት ነው ምክንያቱም የስራና የልማት አመንጭው አንቀሳቃሹ እና ተግባሪው ክፍል ደህንነቱና ሰላሙ የተጠበቀለት ሲሆን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ የእያንዳንዱ ግለሰብና ቤተሰብ ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና መረጋገጥ ስለሚገባው ቅድሚያ ለሰላምና ደህንነቱ በመስጠት የኑሮ ዉድነቱን የመቆጣጠር እና የልማቱን ጉዳይ ደግሞ ጎን ለጎን በአዲስ መልክ እየተለሙ መቀጠል ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ ላይ እንዳለን ይሰማናል ብለዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ሳንፈልግ ተገደን የገባንበትን ጦርነት ድል በማድረግ የከተማችንን ሠላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ምዕላተ ህዝቡን ያሳተፉ ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንሰራለን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ተግዳሮት የሆኑ አደረጃጀቶች እና የታጠቁ ኃይሎች በከተማችን ምንም ዓይነት ሕገ ወጥ ተግባር ላይ እንዳይሠማሩ ለማድረግና ከመንግሥት ውጪ ማንኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀት ይሁን ኃይል ትጥቅ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራዎች እንሰራለን ያሉት አቶ ዘውዱ።
የህዝባችንን ደህንነት በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ አደጋ ላይ የማይወድቅባትን ከተማ ለመፍጠርና የሕግ የበላይነትን በሚታይና በሚጨበጥ ደረጃ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሰፋፊ ሥራዎች ተጠናክረው፣ ዜጎች የደህንነት ስሜ ታቸው እንዲጎለብት ለማድረግ በትኩረት የምንሰራ ይሆናል ብለዋል።
ከተማዋን ከሁለንተናዊ ኋላቀርነት ለማላቀቅና የኢኮኖሚ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሰዉ ሰራሽ የኑሮ ዉድነት ለመቆጣጠር በመንግሥት የተጀመሩ ሥራዎችን በማስቀጠልና አዳዲስ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን በመቀየስ ሰፊ ሥራዎች የምንሰራ ይሆናል በማለትም ከተማዋ ያላት የኢኮኖሚ ምንጮች በዝርዝር በማጥናት ልማቷን ማፋጠን ተቀዳሚ ስራችን ይሆናል ብለዋል፡፡
በተለይ አሁን ባለንበት የዘመቻ ህልውና የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ችግር በከተማችን ኢኮኖሚ ላይ ድቀትን እንዳያመጣ በቀጣይነት ለመከላከል በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
ለዚህም የሚወሰዱት መፍትሔዎች ዘመቻ ለህልውናው ሊፈጥረው የሚችለውን ተጽዕኖ መቀነስን፣ እንዲሁም የተጀመረው ጦርነት ከተጠናቀቀ በኃላም ኢኮኖሚውን ወደ ጤናማ ሁኔታ መመለስን ታሳቢ ያደረጉ ይሆናሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሆነ የተማረ ወጣት የሰው ኃይል ያለባትን ይህች ከተማ እምቅ ኃይሏን በመጠቀም ለከተማዋ እድገት ዘርፈ ብዙ ሚና እንዳለው አምናለሁ ይህንንም አስቀድሞ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በከተማችን ለዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት መዋል ሲገባቸው ተጓተው የህዝብ ቅሬታ መነሻ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በዝርዝር በመለየት፣ ጠንካራ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋትና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን አጠናቀን ለህዝብ አገልገሎት ለማዋል ከፍተኛ ርብርብ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
በመንግስት ተቋማት ላይ በአስተሳሰብም በተግባርም ያሉ የሌብነትና መልክ ያጣ ግለኝነት ተግባሮችን በመታገል፣ ለሌብነት የሚያመ ቹ የመንግስት አሠራሮችን ለይቶ ማስተካከል፣ እንዲሁም የሚስተዋሉ የሌብነት እኩይ ድርጊቶችን ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ማጋለጥና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ሲቪል ሰርቪሳችን ከሌብነት የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ያሉት ተቀዳሚ ከንቲባው በትምህርትና በጤናው ዘርፍም ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
ለከተማዋ ሴቶችና ወጣቶችም እምቅ አቅማቸውን ተጠቅመው ለለውጥና ለከፍታ እንዲሰሩ ጠይቀው፥ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ የከተማዋ ተወላጆችም ፊታቸውን ወደ ከተማዋ ልማት እንዲያዞሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሙሉጌታ ደሴ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.