Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2011 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱም ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በውይይቱም የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የግዢ ፕሮፎርማ አሰባሰብና የግዥ አፈጻጸም ሂደት፣ የደመወዝ አከፋፈል ማስረጃ የተሟላ አለመሆን፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስልክ ቁጥር  ላልተረጋገጠ ስልክ ክፍያ መፈጸሙ የሚሉት ነጥቦች የኦዲት ግኝት ተብለው በዋናነት የተለዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዋና ኦዲተር ውስንነት ይታይባቸዋል ብሎ የለያቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በመለየትና የተሰጠውን አስተያየትም በግብዓትነት በመጠቀም ችግሮቹን እየገመገመ፣ እያረመ እና የማስተካከያ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሀመድ የሱፍ በበኩላቸው የመንግስት ግዥና ፋይናንስ ስርዓቱን ባልተከተለ መልኩ ግዥና ክፍያ መፈጸም፣ የክፍያ ተመን ሳይኖራቸው ክፍያ መፈጸም፣ የመንግስት ንብረት በአግበቡ አለመያዝና የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መኖሩ በኦዲት ግኝቱ የተለየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የበጀት አያያዝና የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ ከዋና ኦዲተር እና ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን በግብዓትነት በመውሰድ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.