Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው በደብረ ብርሃን የከተማዋን ኢንቨስትመንት የሚመጥን መሠረተ-ልማት ሊሟላ እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደብረ ብርሃን የከተማዋን ኢንቨስትመንት የሚመጥን መሠረተ-ልማት ሊሟላ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘውን በውስጡ ስምንት ሼዶችን ያቀፈውን የኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡

ኮሚቴው በፓርኩ ውስጥ የጅንስ ሱሪ እና ሹራብ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ከጎበኘ በኋላ ፥ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ከተማዋን የሚመጥኑ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመገንባት፣ አመራሩ አቅሙን አሟጦ መሥራት አለበት ብሏል።

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ ዶክተር የሺመቤት ደምሴ ፥ ሰሞኑን የመስክ ምልከታ በተደረገባቸው የባሕርዳር እና የኮምቦልቻ እንዲሁም በደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ ኃላፊዎች የመሠረተ-ልማት ችግር በስፋት እየተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፓርኮቹ አመራሮች ከክልሉ ጋር በቀጥታ በመገናኘት ልዩ ትኩረት እና ክትትል ተደርጎላቸው ችግሮቻቸው በፍጥነት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡

የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ አጠቃላይ ችግሮቹ እንዲፈቱ ከተማ አስተዳደሩ ማገዝ እንዳለበት አስገንዝበው ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መንግስት ባፈሰሰው የመዋዕለ ንዋይ ልክ እየለሙ ስላልሆነ ቅድሚያ መሟላት ላለባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በኢንዱስትሪው አካባቢ የደረቅ ወደብ ጉዳይ፣ የፈጣን መንገድና ተጨማሪ የኃይል መቀበያ ንዑስ ጣቢያ ጉዳዮች በፌዴራል ደረጃ እንዲፈቱ ለሚመለከተው የፌዴራል መሥሪያ ቤት በማሳወቅ ግፊት ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

የደብረብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት ፥ የከተማዋን ኢንቨስትመንት የሚመጥን መሠረተ-ልማት አቅርቦት ባለመኖሩ በአሁኑ ሰዓት 136 ፕሮጀክቶች መንገድ አልባ ሲሆኑ ፥ ከእነዚህም 77 ፕሮጀክቶች አማራጭ መንገድ የሌላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም ፥ 281 ፕሮጀክቶች የመብራት አቅርቦት የሚፈልጉ መሆናቸውን፣ ፍላጎቱ አሁን ካለው የኃይል ማሠራጫ ጣቢያ በላይ መሆኑን እንዲሁም 9 ፕሮጀክቶች ማሽነሪ ተክለው በመብራት አቅርቦት ችግር ወደ ማምረት መሸጋር አለመቻላቸውን ጠቅሰው፣ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከተው የፌዴራል መሥሪያ ቤት ጋር በመነጋጋር ችግሮችን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከባንክ እግድ ጋር በተያያዘ በባንክ ዋስትና ተይዘው ብድር በሚወስዱ ፕሮጀክቶች ላይ መንግስትም፣ ባንኮችም እርምጃ ሲወስዱ የአፈጻጸም ግልጸኝነት ባለመኖሩ ቀጣይ እንዲስተካከሉ ኮሚቴው እንዲያግዝ መጠየቃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.