Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው በፍርድ ቤቶች የቀጠሮ መራዘም ችግር እንዳለ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፍርድ ቤቶች የቀጠሮ መራዘም ችግር መኖሩን ገለፀ።

ቋሚ ኮሚቴው በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ያደረገውን የመስክ ምልከታ አስመልክቶ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

በውይይት መድረኩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊን ጨምሮ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በምልከታው ተቋማቱን ለማሻሻል ያስፈልጋሉ የተባሉ አዋጆች መዘጋጀታቸው እና ጥናቶች በሂደት ላይ መሆናቸውን በጥሩ ጎኑ ገምግሟል።

በሚዘጋጁ ህጎች እና እየተዘጋጁ ባሉ ሰነዶች ዙሪያ ዳኞች ሊሳተፉ እንደሚገባም በውይይቱ መነሳቱን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እንዲሁም በየጊዜው ከህብረተሰቡ የሚመጡ ቅሬታዎችን ለመፍታት አመራሩ ጥረት እያደረገ ያለ ቢሆንም፤ የቀጠሮ መራዘም ችግር እንዳለ እና ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ግልባጭ ሊኖር እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል።

ከተቋማቱ ሰራተኞች ጋር ባደረገው ውይይት የቋንቋ ትርጉም ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ይህን አገልግሎት የሚሰጥ በተቋሙ እንደሌለ ማወቅ መቻሉንም አንስቷል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በበኩላቸው፥ በተቋማቱ ሰፊ የሆኑ የማሻሻያ ስራዎች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ሂደት ዳኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በፍርድ ቤቶች ዙሪያ የሚሰሩ ደላሎችን በሚመለከት ችላ እንደማይሉ ጠቁመው፥ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚዘገቡ ዘገባዎች በሚተላለፉበት ጊዜ ተከታትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ የዳኛው ሃላፊነት በመሆኑ ወሳኝ የሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎች ሲወሰዱ ፍርድ ቤቶች ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.