Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል “ህገ መንግስታዊ መብቶች የህገ መንግስታዊ ዋስትና አላቸው” በሚል መሪ ቃል ሲምፖዚየም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በሀረሪ ክልል በዛሬው እለት “ህገ መንግስታዊ መብቶች የህገ መንግስታዊ ዋስትና አላቸው ” በሚል መሪ ቃል ሲምፖዚየም ተካሂዷል፡፡

ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት፥ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም ፈተናዎችን በትዕግስት ፣ በመነጋገርና በሰከነ መንገድ በመንቀሳቀስ በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በተለይ በክልሉ ሁከትና ግርግር እንዲከሰት በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም ከሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብ ጋር በመቀናጀት ሙከራዎቹን በማክሸፍ ሰላምና አንድነት ማጎልበት መቻሉን አንስተዋል፡፡

በቅርቡም ከሀረሪ ጉባኤ መራጮች ጋር ተያይዞም ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱን በመጠቆም፥ በዚህም ውጤት መመዝገቡንና በድል መወጣት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሂደቱ ደካማ ጎኖችን በማረምና ጥንካሬዎችን በማጎልበት በአንድነትና በትብብር መስራት መቻሉ ለውጤቱ ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከተም ነው ያመላከቱት፡፡

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሀረሪ ጉባዔን መራጮችን ተመልክቶ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በሰበር ሰሚ ችሎት የተላለፈው ውሳኔ እና የተገኘው መልካም ውጤት የሀረሪ ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን ለፍትህ ለቆሙ ሁሉ ድል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪን እና የሀረሪ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀረሪ ብሔረሰብ አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.