Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን  ብር በላይ  ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች እየተዘዋወረ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በዛሬው እለት ከአሚር ኑር ወደ አቦከር ወረዳ የተዛወረ ሲሆን ዋንጫው አቦከር ወረዳ ሲደርስም ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በእስካሁኑም ከአምስት ወረዳዎች ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ  ተገልጿል።

በዋንጫው ርክክብ ወቅትም የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እና በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ÷የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሀገራችን የእድገት ውጥኗን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ካሉ ፕሮጀክቶች ቀዳሚው ነው ብለዋል፡፡

ከግድቡ ግንባታ ጅማሮ አንስቶም መላው ህዝብ  ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን በእውቀቱ፣ በገንዘቡና በጉልበቱ በገንዘቡ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በክልሉም በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ወደ ክልሉ ከመጣ ወዲህም ህዝቡ በንቃትና በከፍተኛ መነሳሳት በመንቀሳቀስ ግድቡ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም  በቀጣይም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን ማጠናከር እና የቁጠባ ባህልን ማዳበር ይገባል ብለዋል፡፡

የወረዳ አመራሩም ከሃይማኖት አባቶችን ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጋር በመቀናጀት እና ህዝብን በማነቃነቅ  የአንድነታችን እና የትስስራችን መገለጫ የሆነውን ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ በትኩረት  መንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአቦከር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሱልጣን ሳኒ እንዳሉት ዋንጫው በወረዳው በሚኖረው ቆይታም ህዝብን የማስገንዘብና ገቢ የመሰብሰብ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

ለዚህም የታላቁ ህዳሴ ዋንጫ በወረዳው በሚኖረው የ15 ቀን ቆይታ 350 ሺህ ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው እቅዱን ለማስካትም ርብርብ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተለይ የወረዳው ነዋሪ ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በሚኖረው ቆይታ እንደ ክልል 20 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 8 ሚሊየን ብሩ ከወረዳዎች የሚሰበሰብ መሆኑን መረጃዎች ማመላከታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጥህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.