Fana: At a Speed of Life!

በሀሳብ መሸነፍን በሰላማዊ መንገድ መቀበል የስልጣኔ መገለጫ ነው-የኃይማኖት መሪዎች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀሳብ መሸናነፍን በሰላማዊ መንገድ መቀበል የስልጣኔ መገለጫ መሆኑን የኃይማኖት መሪዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ህብረት መሪዎች በወቅታዊ የሀገሪቷ የሰላም ሁኔታ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም በመጪው ግንቦት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅም ለመራጩ ህዝብና ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርበዋል።

በምርጫ ጊዜ በሰለጠኑት ሀገሮች ያለውን የሀሳብ ፍጭትና የመነጋገር ባህል መቅሰም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የቅዱስ ፓትሪያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሊቀ-ጳጳስ ብጹህ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መራጩ ህዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝቡ የሚበጁ ሀሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ማስተዋወቅ ያለባቸው መሆኑንም አሳስበዋል።

መራጩ ህዝብም በሃቀኝነት በታማኝነት ድምጹን መስጠትና ውጤቱንም በጸጋ መቀበል ይገባዋል ነው ያሉት።

ምርጫውን በሰላም ማጠናቀቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያገኙት የሰላም የኖቤል ሽልማት ለሀገሪቷና ለህዝቦቿ የሚገባ መሆኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሰላምና ትብብር ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሃመድ በበኩላቸው፥ ለምርጫው ሰላማዊነት መራጩም ሆነ ተመራጩ በልበ ሰፊነት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

በሁከትና ብጥብጥ ሀሳብን መግለጽም ለሀገር የሚጠቅም ፍሬ ነገር የማይገኝበት በመሆኑ ከስሜታዊነት ወጥቶ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ አገር ለማስረከብ መትጋት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ፥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን በኃይማኖትና በብሄር ከሚከፋፍሉና ጥላቻን ከሚፈጥሩ ቅስቀሳዎች ሊቆጠቡ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግም በሀገሪቷ እየተስተዋሉ ያሉ አንዳንድ ግጭቶችን በአፋጣኝ ማስቆም ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።

ምርጫ የዜጎችንም ሆነ የሀገርን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ የሚወስን በመሆኑም መራጩ ህዝብ ስለሚመርጠው ፓርቲ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ከወዲሁ መስራት ይገባልም ብለዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የሲቪክ ማህበራትና ምሁራንም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኃይማኖት መሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.