Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ዜጋ አጀንዳ የሚያስይዝበት አሰራር እንደሚዘረጋ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ የሚያስይዝበት አሰራር እንደሚዘረጋ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የውይይት ሃሳቦች ከታች ወደ ላይ እንደሚሰበሰቡ አስረድተዋል።

በውይይቱ ይህ ይነሳ ያ አይነሳ የሚባል ነገር የለም ያሉት ሰብሳቢው÷ ኮሚሽኑ በአጀንዳዎች ላይ ጣልቃ አይገባም ብለዋል።

ምክክሩ ልሂቁ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ባለመሆኑም ሁሉም ዜጋ ሐሳቡ በጥቂቶች እንዳይጨናገፍ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ በየክልሉ እንደ አመቺነቱ ጽሕፈት ቤቶች እንደሚቋቋሙ ያነሱት ፕሮፌሰር መስፍን፥ የኮሚሽኑ ምክር ቤት መርሃ ግብር ያዘጋጀ ሲሆን ስትራቴጂክ ዕቅዱን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ግብዓት እንደሚሰበሰብም አመላክተዋል።

አጀንዳ የመሰብሰብ ሥራው በገጽ ለገጽ ማህበረሰቡ በሚረዳው ቋንቋ ስለ ኮሚሽኑ በማስረዳት ሃሳቡን እንዲገልጽ ይደረጋል ያሉት ሰብሳቢው፥ በሌሎች አማራጮችም በስልክ፣ ኢሜይል እና ፖስታ በመሳሰሉት ማቅረብ እንደሚቻል አብራርተዋል።

ማሕበረሰቡ ሃሳቡን ከማቅረብ በተጨማሪ በማዕከል ደረጃ ለሚደረገው ምክክር ወኪሎቹን እንዲመርጥ ይደረጋልም ነው ያሉት።

የአጀንዳ ሃሳቦች መሰብሰብ የሚጀመርበት ጊዜም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገልጸዋል።

በታደሰ ሽፈራው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.