Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴው ግድብ ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችን ለመከላከል የምዕራብ ዕዝ ከመቼውም ጊዜ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል-ብ/ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የህዳሴው ግድብ ህልውናችን በመሆኑ በግድቡ ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችና ጥቃቶችን ለመከላከል የምዕራብ ዕዝ ከመቼውም ጊዜ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉየዕዙ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀው ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ተናገሩ፡፡
የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ ሠራዊቱ ዝግጁነቱን አረጋግጦ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
ጄኔራል መኮንኑ የውሃ ሙሌቱን ማንም የውጪ ኃይል አያስቆመውም፤የሰራተኞቹ ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይጠበቃል፤ስራው ያለምንም እንቅፋት እንዲከናወንም በየደረጃው ያለ የሰራዊት አባል ከሌሎች ተጓዳኝ የጦር ክፍሎች ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
እንዲሁም መጪው አገራዊ ምርጫ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ፀጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ ዕዙ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉንም ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የመተከል ዞን ሰላምን ወደ ነበረበት ለመመለስ የዞንና የወረዳ ኮማንድ ፖስቶች በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀው የህዝቡን ሞትና መፈናቀል ለማስቀረት የፀጥታ ኃይሉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት፡፡
ሠራዊቱ ለህዝቡ ሲል ቆስሏል መስዋዕትነትም ከፍሏል፤ መስዋዕትነቱ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለሰጡት ተልዕኮ የተከፈለ ነው በማለትም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ተሃድሶ ማዕከል ገብተው በስልጠና ላይ የሚገኙ ታጣቂዎችን ከሕብረተሰቡ ጋር የማቀራረብ ስራ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.