Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መዳፈር ለማንም አይጠቅምም – መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የመልማት ፍላጎትና መብት፤ ስራውም የሉዓላዊው ህዝብ የላብ ውጤት ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ህዳሴ ግድቡ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ያለ ማንም ዕርዳታና ድጋፍ የተገነባ ከፍፃሜ ሊደርስ የተቃረበ የማንነት ፕሮጀክት ነው፡፡

ህዳሴ ግድቡንም ሆነ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መዳፈር ለማንም የማይጠቅም መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች፣ ወደፊትም የምትኖር ታላቅ ሀገር ናት ሲሉም ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የገለፁት፡፡

ፕሮጀክቱ ላይ የሚሰጥ ማንኛውም አፍራሽ ሀሳብ ለማንም የማይጠቅም፣ ሉዓላዊነትን የሚጋፋና የህዝቦችን ነፃነትና የመልማት ፍላጎት የተጋፋ ነውም ብለውታል፡፡

ኢትዮጵያ በናይል ላይ ፍትሀዊና የጋራ ተጠቃሚነትን ባከበረ መልኩ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን ያነሱት አምባሳደር ዲና፥ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ባለፉት አመታት ስታካሂዳቸው የነበሩ ድርድሮችም የዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2010 የተፈረመው ስምምነት ስድስት ሀገራትን ያካተተ፤ የከዚህ ቀደሙን የቅኝ ገዥ ስምምነት ያስቀረ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ሀገራትን የሚበጀው ምክንያታዊና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንጂ ሉዓላዊነትን መጋፋት አይደለምም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት አልምታ የመጠቀም ፍላጎትና መብቷን ማንም ሊነጥቃት አይችልም፤ ስጋቱም የለባትም ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡

ኢትዮጵያ ለድርድር፣ ፍትሀዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት እንደ ከዚህ ቀደሙ ትሰራለች፤ ከዚህ ውጪ በህዳሴ ግድቡ ላይ በማስፈራሪያና በዛቻ የሚመጣ ለውጥ እንደማይኖርም ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ ላይ ከስምምነት ሊደረስባቸው የሚገቡ የቀሩ ሀሳቦች በድርድርና በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ስራ መፍትሄ እንደሚያገኙም አስረድተዋል፡፡

ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ አሁንም አቋሟ መሆኑን የገለፁት አምባሳደሩ፤ ለአፍሪካዊ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች እንዲገኙ ይሰራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በድርድር ለመፍታትና ሁሉንም በጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም መስራቷን እንደምትቀጥልም አውስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.