Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሶስትዮሽ ውይይት ውጪ ሌሎች ምክረ ሀሳቦችን አትቀበልም

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሶስትዮሽ ውይይት ውጪ ሌሎች ምክረ ሀሳቦችን እንደማትቀበል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በዛሬው ዕለት ለካቢኔ አባላት እና ለባለድርሻ አካላት የግድቡን አሁናዊ ገፅታ እና በግብፅ ወቅታዊ አቋም ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም የግድቡን አሁናዊሁኔታ እና የወደፊት እቅዶች ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ በዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በትኩረትና በተገቢው ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል እየተደረገ ባለው ውይይት ዙሪያም ሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል።

በዚህም ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የቀጣናውን እና የተፋሰሱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናከር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ግን ግብጽ ከሶስትዮሹ ውይይት ውጪ በሱዳን ካርቱም በተደረገው ውይይት ላይ ያቀረበችው ምክረ ሃሳብ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጥስ መሆኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

ግብጽ ባቀረበችው ምክረ ሀሳብ ላይም በየዓመቱ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ ይለቀቅልኝ ማለቷ እና የአስዋን ግድብ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 165 ሜትር ሲደርስ ኢትዮጵያ ውሃ መልቀቅ አለባት፤ እንዲሁም ሶስተኛ ወገን በአደራዳሪነት ይግባ የሚል አቋም ማቅረቧን አንስተዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት፥ ግብፅ ያቀረበችው መክረ ሃሳብ ኢትዮጵያ በውሃው ላይ ያላትን መብት የሚጥስ እና ብሄራዊ ጥቅሟን የሚጎዳ በመሆኑ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የምትቀበለው አይሆንም ብለዋል።

ይህን ተከትሎም ግብጽ በጉዳዩ ዙርያ የኢትዮጰያን ስም በአለም አቀፍ መድረኮች በማጥፋት እና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም በዲፕሎማሲያዊ እና በሌሎች የልማት አጋሮቸ ዘንድ ጥርጣሬን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጰያ በግድቡ ዙርያ አለምአቀፍ መመሪያዎችን የትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ እየተጓዘቸ መሆኑን ጠቅሰው፥ በግብፅ በኩል የሚመጡ ፍላጎቶች ግን እነዚህን መመሪያዎች ያላከበሩ፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አስመልከቶ ሀገራት በፍትሃዊ መልኩ መጠቀም እንደሚገባቸው የሚጠይቅውንም የጋራ መግባባብትም የጣሰ መሆኑን ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው፥ ግብፅ ጉዳዩን አሁን ላይ የሞት ሽረት ያደረገቸው የግድቡ ግንባታ እየተፋጠ መምጣቱን ተከትሎ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ግለትን ለመጠቀም ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፥ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጉዳይን ፖለቲካዊ ያላደረገችው በቴክኒካዊ መንገዶች መፈታት ስለሚገባቸው ነውም ብለዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተርባይኖች ቅነሳ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ በግድቡ ለመግጠም ከታሰቡ ተርባይኖች ውስጥ ሶስቱን ለመቀነስ መታቀዱን አንስተዋል።

በዚህም በግድቡ በሚተከሉ 16 ተርባይኖች 6 ሺህ 350 ሜጋዋት ውሀ እንደምታመነጭ ተቀመጦ እንደነበረ አስታውሰው፤ አሁን የሚደረገው የሶስት ተርባይኖች ቅነሳ የግድቡን ሀይል የማመንጨት አቅም አይቀንሰውም ብለዋል።

ምክንያቱም ትርባይኖቹ ቢገጠሙ የማመንጨት አቅማቸው 30 በመቶ ብቻ ነው፤ 13 ሲሆን ግን የሚቀነሱትን ተርባይኖች አቅም ወደ ሚተከሉት በማድረግ የማመንጨት እቅማቸውን 35 በመቶ ማድረስ ያስችላልም ብለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ 100 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማዳን እንደሚቻል የገለፁ ሲሆን፥ ከዚህ ወጪ በየዓመቱ ይመነጫል ተበሎ የተቀመጥው የኃይል መጠን እንደማይቀንስም አብራርተዋል።

በብስራት መለሰ እና ዳዊት በሪሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.