Fana: At a Speed of Life!

በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 132 ሺህ 860 የአሜሪካን ዶላር ተያዘ – የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 132 ሺህ 860 የአሜሪካን ዶላርና 9 ነጥብ 2 ኪሎግራም የሚመዝን ኮኬይን መያዙን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ከአገር ሊወጣ የነበረው ዶላር መድረሻውን ዝምባብዌ ያደረገ ሲሆን ግለሰቡን በቴክኖሎጂ በተደገፈ ጥብቅ ፍተሻና ክትትል በቁጥጥር ሥር መዋሉ ነው የገለጸው፡፡

የዚምባብዌ ዜግነት ያለው ይህ ግለሰብ መስከረም 15 በኢኳቶሪያል ጊኒ በኩል የገባ ሲሆን በነጋታው ወደ ዚምባብዌ ሊያመራ ነበር ተብሏል፡፡

ግለሰቡ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የተጠቀሰውን መጠን ያህል ዶላር መያዙን ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አለማድረጉ ተሰምቷል፡፡

ከዶላሩ በተጨማሪ በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከአዲስ አበባ ወደ ናይጄሪያ ሊጓጓዝ  የነበረ ግምቱ 920 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ 9 ነጥብ 2 ኪሎግራም የሚመዝን ኮኬይን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ተገልጻል፡፡

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በህገወጥ ድርጊቱ ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦች በኢትዮጵያ ለቀናት ባደረጉት ቆይታ  ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ግንኙነት በመፍጠር በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር ብሏል፡፡

ኮኬይን የያዘው ግለሰብ መስከረም 8 ከናይጄሪያ ወደ አዲስ አበባ የገባ ናይጄሪዊ መሆኑ ተግልጻል፡፡

ግለሰቡ መስከረም 18 ቀን ኮኬይን በመያዝ ከአዲስ አበባ ወደ ናይጄሪያ ይዞ ለመጓዝ ሲሞክር ነው በቴክኖሎጂ በተደገፈ ጥብቅ ፍተሻና ክትትል በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው ተብሏል፡፡

በህገ ወጥ ተግባር የተጠረጠሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ከቦሌ ኤርፖርት የጉምሩክ  ኮሚሽን ቅርንጫፍና  ከፌደራል ፖሊስ  ኮሚሽን ጋር በትብብርና በቅንጅት ፍተሻዎችን በማጠናከር መሰራቱን መረጃ  ይጠቁሟል።

በህገ ወጥ  የገንዘብና  የአደገኛ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ድርጊት የተሳተፉት ተጠርጣሪዎች እንዲሁም እጅ ከፍንጅ የተያዙት የገንዘብ ኖቶች እና አደንዛዥ እጹ  ለተጨማሪ ምርመራ ለፌደራል  ፖሊስ ኮሚሽን  የወንጀል ነክ ዲፓርትመንት  መላካቸውም ተመልክቷል።

በአገሪቱ  እየተደረገ ካለው የገንዘብ ቅያሪ ጋር  በተያያዘ  የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶችን ለመግታት  በቅንጅት የሚሰራ ግብረሃይል መቋቋሙን ያስታወሰው ብሄራዊ  መረጃና ደህንነት  አገልግሎት፤በተለያዩ  የመግቢያ መውጫ ኬላዎች ጥብቅ፣ ተከታታይና በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትል  እያደረገ እንደሚገን ተግልጻል፡፡

በህገ  ወጥ  መንገድ  የሚዘዋወሩ የኢትዮጵያና የተለያዩ የውጭ  አገራት የገንዘብ ኖቶች፣ አደንዛዥ እጾችና ሌሎችንም ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ለመግታት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞችና አመራሮች ሌት ተቀን  እየሰሩ መሆናቸውን ያመለከተው መግለጫው፤ ህብረተሰቡ ከህገ ወጥ ድርጊቶቹ ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለመረጃና ለጸጥታ አካላት እየሰጠ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.