Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)በህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስትዳደር ገለጸ።

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በሰጡት መግለጫ÷ ባለፉት አራት ወራት የመሬት ወረራ አስመልክቶ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከፍተኛ አመራሮች የተካተቱት ቡድን ተዋቅሮ ባካሄደው ጥናትም ለአርሶአደሩ የመሬት አጠቃቀም የተዘጋጀ መመሪያን በህገወጥ መልኩ በመጠቀም ከ20 ነጥብ 7 ሄክታር ስፋት ያላቸው 497 ቦታዎች በህገወጥ መልኩ ተላልፈው ተገኝተዋል።

383ነጥብ32 በሄክታር ስፋት ያላቸው 457 ወደ መሬት ባንክ መግባት ሲገባቸው ሳይገቡ መብት ለሌላቸው አካላት ተላልፈው ተገኝተዋል።

አቶ ጥራቱ እንደተናገሩትም÷ ህገወጥ የመሬት ወረራው ለህብረተሰቡ የጋራ ጥቅም ተብሎ ለአረንጓዴ አካባቢ በተለዩ አካባቢዎች ላይም ተፈፅሟል።

ይዞታዎቹ አርሶአደር ላልሆኑና የልማት ተነሺ ላልሆኑ ግለስቦች እንደሆኑ ተደርጎ ሰነድ በማዘጋጀት፣ አርሶ አደሩን በማታለል እና በማስገደድ ፋይላቸው ውስጥ የማይገባቸው ስሞች እንዲካተቱ በማድረግ የተወረሩ ናቸው።

ድርጊቱን ከመዋቅሩ የተባረሩ አካላት ውስጥ ካሉ ፈፃሚዎችና ባለሞያዎች እንዲሁም ከደላሎች ጋር በመረዳዳት እንደፈፀሙትም ተረጋግጧል።

በዚህ ህገወጥ የመሬት ወረራ ላይ የተሳተፉ አካላትን የመለየቱና ለህግ የማቅረቡ ስራም መጀመሩን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የካዳስተር ስርዓቱን ወይም እያንዳንዱ ቁራሽ መሬት ተመዝግቦ የሚያዝበት ስርዓትን መተግበርና የመሬት ልማት አስተዳደር አደረጃጀቱን የማስተካከል ስራ እየተሰራ ነው።

በትእግስት ስለሺ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.