Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሰዎች ህይወት እንዲጠፋ ያደረገው ግለሰብ በሞት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የ5 ሴት ወጣቶች ህይወት እንዲጠፋ ያደረገው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ  ዳኛ አቶ ሐኪም ሲራጅ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት  አብዱከሪም ጣሂር አብደላ የተባለው ግለሰብ ነዋሪነታቸው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉርሱም ወረዳ ዳይፈርስ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የሆኑ ወጣት ሴቶችን በህገ ወጥ መንገድ በማስኮብለል ለህልፈተ ህይወት በመዳረጉ ቅጣቱ ተላልፎበታል ።

“በጎረቤት አገር በኩል ሳውድ አረቢያ ወስጄ በከፍተኛ ደመወዝ ስራ እንድትቀጠሩ አደርጋለሁ ” በሚል ማታለያ በ2010 ዓም በተለያዩ ቀናትና ወራት ከቀያቸው ካስኮበለላቸው 8 ወጣት ሴቶችን ላይ ከእያንዳንዳቸው 3 ሺህ ብር ተቀብሏል ።

ስልክ በመደወልና  ዘመድ አዝማድ ሳይሰማ ከአደጉበት ቀዬ ጭለማን ተገን በማድረግ ካስኮበለላቸው 8 ሴት መካከል በጀልባ መስጠም ምክንያት 5ቱ ህይወታቸው ማለፉን ዳኛው ገልፀዋል ።

በተጨማሪም በደላላ አማካኝነት ቤተሰቦቻቸውን በማስጨነቅ ከእያንዳንዳቸው ቤተሰብ 10 ሺህ ብር  መቀበሉን ተናግረዋል።

ከአደጋው የተረፉት  ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ ለሟች ዘመዶች በሰጡት ጥቆማ መሰረት የክስ አቤቱታ የደረሰው የጉርሱም ወረዳ ፖሊስ ወንጀለኛውን አብዱከሪም ጣሂር አብደላ በቁጥጥር ስር በማዋል ክስ ተመስርቶበት የምርመራ መዝገቡ አጣርቶ ለማየት ስልጣን ላለው ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲተላለፍ ተደርጓል።

ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ግለሰቡ ወንጀሉን መፈጸሙ በአቃቢ ህግ፣በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማረጋገጥ የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ከመረመረ በሃላ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሲል አምራች ሐይል በሆኑት ወጣት ሴቶቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት አሰቃቂ ወንጀል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጥር 2 ቀን 2012 በዋለው  ችሎት ወንጀለኛው አብዱከሪም ጣሂር አብደላን በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈፃሚ የሚሆነው ለሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ቀርቦ ይሁንታ ሲያገኝ ብቻ ነው ተብሏል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.