Fana: At a Speed of Life!

በሕገወጥ የዶላር ዝውውር የተጠረጠሩ 70 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በሕገ ወጥ ተግባራት የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገወጥ የዶላር ዝውውርና በሃዋላ የተጠረጠሩ 70 የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ 70 የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ኑሯቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ አድርገው በሕገወጥ የዶላር ዝውውር ሲሳተፉ በተደረገ ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል ተደርሶባቸዋል፡፡
 
ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የሚላክ ዶላር፣ ዩሮ እና የተለያዩ ሀገራት የውጭ ገንዘቦችንም በየሀገራቱ ለዚሁ ዓላማ ባስቀመጧቸው ወኪሎቻቸው አማካይነት ወደ ግል አካውንታቸው እንዲገባ በማድረግና የኢትዮጵያ የብር ኖቶችን በመስጠት በሕገወጥ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ተግባርም ጭምር በመሳተፋቸው ተጠርጥረው ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት የሠጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው እና ከሕገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር ሕገወጥ የመኖሪያ ፈቃድን እና ፓስፖርት ጭምር አጭበርብረው ሲሰጡ የነበሩ 36 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውም ተገልጿል፡፡
 
በአዲስ አበባና ሐዋሳ ከተሞች በኢሚግሬሽንና ኤርፖርት አካባቢዎች ላይ ተመድበው ሲሰሩ ከሕገ ወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር የግል ጥቅማቸውን ሲያግበሰብሱ የነበሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች እንዲሁም ሕገወጥ ደላሎች በተደረገ ጥብቅ ክትትልና የሕዝብ ጥቆማ ከሲዳማ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አገልግሎቱ በመግለጫው ጠቁሟል።
 
ተቋሙ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በድሬዳዋ አካባቢ በሕገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎች ላይ ያደረገውን ጥልቅ ጥናት መሰረት በማድረግ፥ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የተቀናጀ ኦፕሬሽን በማካሄድ ግምታቸው ከ100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆኑ የማዕድን ምርቶችን ከ11 ሕገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎችር ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉንም አመልክቷል።
 
በተያያዘ በኮንትሮባንድ ንግድ በመሰማራት ግምታቸው ከ70 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን፣ ልባሽ ጨርቆችን፣ የሲጋራ ምርቶችና መሰል ቁሳቁሶችንም ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉንም አገልግሎቱ ጠቅሷል።
 
በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት አስፈላጊውን መረጃ በመሰብሰብ ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግም በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 582 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ 58 ሺህ ዩሮ፣ 10 ሺህ ፓውንድ፣ 5 ሺህ 530 የካናዳ ዶላር ፣ 145 የሳውዲ ሪያል ገንዘቦች እንዲሁም ከ2 ሚሊየን 300 ሺህ ብር በላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ እና 10 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ወርቅ ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉንም ነው አገልግሎቱ የገለጸው።
 
ባለፉት ወራት ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተካሄዱ ተከታታይ ኦፕሬሽኖች÷ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከልም ከህወሓት የሽብር ቡድን ተልዕኮ በመውሰድ ለቡድኑ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ 33 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም እየተወሰዱ ባሉ የሕግ ማስከበር እርምጃዎች፣ ከ200 በላይ የሽባሪው የሸኔ የከተማ ህዋስ አባላት ወይንም ተላላኪዎች መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡
 
ለሽብር ቡድኑ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ የ20 ግለሰቦች የባንክ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲቋረጥ መደረጉንም አገልግሎቱ አስታውቋል።
 
የጽንፈኝነት አስተሳሰብን በማራመድ የሕዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሃሰትና የውሸት ወሬዎችን በመንዝናት ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩ ሌሎች 42 ተጠርጣሪ ግለሰቦች መያዛቸውም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
 
ሀገሪቱ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን ዝውውር ለመቆጣጠርና ለመከላከል ያወጣችውን አዋጅ መሠረት በማድረግ በተከናወኑ የተቀናጁ የኦፕሬሽንና የፍተሻ ሥራዎችም 11 ብሬን የቡድን የጦር መሣሪያዎች፣ 524 የነፍስ ወከፍ የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 31 ሽጉጦችና 25 ሺህ 656 የተለያዩ የጦር ማሣሪያ ጥይቶች ከበርካታ ተጠርጣሪዎች ጋር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቁሟል።
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ፣ ከፌደራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሽብርተኞቹ፣ በታጣቂዎች እንዲሁም በተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል፡፡
 
ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት የአገልግሎት መስሪያ ቤቱን ነፃ የስልክ ጥሪ 910 በመጠቀም የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.