Fana: At a Speed of Life!

በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይናንስና ንግድ ነክ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን የተለያዩ የህገ-ወጥ ገንዘቦችን በማዘጋጀት፣ በመገልገልና በማዘዋወር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገለፀ፡፡

ፖሊስ  ባደረገው ምርመራ የተቀየረው የብር ኖት 174 ሺህ 350 ብር እንዲሁም 605 ሺህ 550 ሐሰተኛ የኢትዮጵያ ብር በማዘጋጀት፣ በመገልገልና በማዘዋወር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ሰባት መዝገቦችን በማደራጀት እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡

ፖሊስ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ስምንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ስድስት መዝገቦችን አደራጅቶ የምርመራ ሂደት አጠናቆ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ በመላክ ክስ እንዲመሰረትባቸው የተደረገ መሆኑን በቀሪው አንድ መዝገብ ላይም ምርመራ እያጣራ መሆኑን በፋይናንስና ንግድ ነክ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ሽመልስ ጥበቡ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ 99 ሺህ 852 የአሜሪካን ዶላር፣ 3 ሺህ 555 ድራም፣ 210 ዩሮ፣ 2 ሺህ 553 ሪያል፣ 5 ሺህ 495 የሱዳን ገንዘብ፣ 1 ሺህ 800 የኤርትራ ናቅፋ ፣500 የደቡብ አፍሪካ ራንድ እና ከ474 ሺህ 500 ብር በላይ በተደረገ ብርበራ የተያዘ መሆኑን ገልጿል፡፡

ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ 10 መዝገቦችን በማደራጀት እያጣራ ሲሆን እንዲሁም ባደረገው ተጨማሪ ክትትል 14 ሺህ 800 ሐሰተኛ የአሜሪካ ዶላርና ከ1 ሺህ ባለይ ትክክለኛ የህንድ ገንዘብ ይዞ በተገኘው በአንድ ግለሰብ ላይ የምርመራ መዝገቡን በማጠናቀቅ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ መላኩን አቶ ሽመልስ ጥበቡ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በተያያዘም ሁለት የላይቤሪያና ሁለት የካሜሩን ዜግነት ያላቸው በአዲስ አበባና በጅማ ከተማ ትክክለኛ ገንዘብ እናባዛለን በማለት በህብረተሰቡ ዘንድ የማጭበርበር ተግባር ሲፈፅሙ በተደረገባቸው ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው በ3 መዝገብ ምርመራ እያተጣራባቸው መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ፖሊስ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል የህይወት መስዋዓትነት ጭምር እየከፈለ ሃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ቢሆንም ድርጊቱ በሁሉም የሀገራችን ክልሎች የተሰራጨ መሆኑን የተጠቀሰው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ባስተላለፈው መልዕክት ወቅቱ የበዓል ግብይት የሚፈፀምበት በመሆኑ ሐሰተኛ የኢትዮጵያ ብር ከትክክለኛው የሚለይበት የደኅንነት መለያ ምልክቶች ስላለው ህብረተሰቡ በማየትና በዳሰሳ በመለየት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትና አጠራጣሪ ነገር ካጋጠመ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ማሳሰቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.