Fana: At a Speed of Life!

በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ሰብኣዊ መብታቸው እየተጠበቀ መሆኑን ለመርማሪ ቦርዱ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣2013(ኤፍ ቢ ሲ) በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙ የህወሃት ከፍተኛ አመራሮችን ያነጋገረ ሲሆን፤ ሰብኣዊ መብታቸው እየተጠበቀ መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ በትግራይ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ለሚመረምረው ቦርድ ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቦርዱ የማጣራት ስራውን በአዲስ አበባ በሚገኝ የተጠርጣሪዎች ማረፍያ በአካል ተገኝቶ ያከናወነ ሲሆን፤ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ባልጠበቁት ደረጃ ተገቢ የሆነ ሰብዓዊ አያያዝና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ለመርማሪ ቦርዱ አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ተገቢ የሆነ የምግብ፣ የንጽህና፣ የአልባሳትና የመኝታ አገልግሎትን ጨምሮ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ በመደረጉ ለፌደራል ፖሊስ አባላትና አመራሮች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው እንዲሁም የወር ደሞዛቸው በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ለመርማሪ ቦርዱ አባላት አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ተጠርጣሪዎች የወንጀል ህጉ በሚያዘው አግባብ በፍጥነት ወደ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን በመግለጽ፤ መርማሪ ቦርዱ ጉዳዩን አጣርቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

የመርማሪ ቦርዱ አባላት በበኩላቸው ለተጠርጣሪዎቹ እየተደረገ ያለው ሰብኣዊ አያያዝ የሚያስመሰግን በመሆኑ፤ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ያነሷቸውን ቅሬታዎች ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረው ለመፍታት እንደሚጥሩ የገለጹት የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ፤ የፍርድ ቤት ቀጠሮን በተመለከተ ግን ከኮሚሽኑ የወንጀል ምርመራ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.