Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል ፈቃድ ሳይኖራቸውና ግብር ሳይከፍሉ ሲነግዱ የተገኙ 720 የንግድ ሱቆች ታሸጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ፈቃድ ሳይኖራቸውና ግብር ሳይከፍሉ ሲነግዱ የተገኙ 720 የንግድ ሱቆች መታሸጋቸውን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሠሚራ ዩሱፍ በክልሉ እየተበራከተ የመጣው ህገ ወጥ እና ያለፈቃድ የሚካሄድ የንግድ ሥራ በህጋዊ ነጋዴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ለማቃለል በክልሉ ከሁሉም መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሰዎችን በአባልነት ያቀፈ ግብረ ሃይል በማቋቋም ግብር በአግባቡ በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ለሶስት ሳምንታት በተካሄደ ሥርዓት የማስያዝ እንቅስቀሴ ፈቃድ ሳይኖራቸውና ግብር ሳይከፈሉ ሲነግዱ የተገኙ 720 የንግድ ሱቆች በህግ አግባብነት እንዲታሸጉ መደረጉን አስረድተዋል።

ከመካከላቸውም 405 ንግድ ፈቃድ በማውጣት ወደ ግብር ከፋይነት መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪዎቹም የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው በተመሳሳይ ሥርዓት ለማስያዝ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ግብረ ሃይሉ ባከናወነው ሥራ ከማስታወቂያ፣ መደብ፣ ከዓመታዊ የንግድ ትርፍና ሌሎችም የገቢ ምንጮች ሳይከፈል የቆየ ከ34 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም ጠቁመዋል።

ከ13 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ያሉት የሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከቀጥተኛ፣ ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስና ሌሎችም የገቢ ምንጮች ከ361 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.