Fana: At a Speed of Life!

በሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ሀብቶች ላይ ተጨማሪ ጥቆማ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣ በውክልና በሌሎች መንገዶች ተይዘው በሚገኙ ሀብቶች ላይ ጥቆማ እንዲቀርብ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥሪ አቀረበ፡፡

የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት፣ በራሳቸዉ በቤተሰቦቻቸዉና በቅርብ ሰዎች ስም የያዙት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኝ ንብረት ላይ ማቅረብ እንደሚቻል ፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህወሃት የሽብር ቡድን በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በጥፋት ቡድኑና አባላቱ ላይ የወንጀልና የሃብት ምርመራዎች ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በወንጀል የተገኘና በሃገር ውስጥ ወይም በውጭ ሃገር የተደበቀ ሀብት ላይ ጥቆማ እንዲቀርብ በቀረበው ጥሪ መሰረት ከሕዝብ የተሰጡ ብዛት ያላቸው ጥቆማዎችና መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የአሸባሪ ድርጅቱንና አባላትን ሃብት ጨምሮ በተደረገው የማጣራት ሥራ በርካታ ዉጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ለዚህም ተቋሙ ለሕዝቡ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ፣ በቤተሰቦቻቸውና በቅርብ ሰዎች ስም በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ያሉ የማይንቀሳቀሱና ተንቀሳቃሽ ቋሚ ንብረቶችን በአካል በመለየት የጥፋት ቡድኑ ንብረቶችንና ከንብረቶቹ የሚገኘውን ገቢ ለሽብርና ሌሎች ወንጀሎች መጠቀም እንዳይችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ የመከላከል ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ለፋይናንስ ደህንነት ማዕከል፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴርና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ላሳዩት የሥራ አጋርነት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡

ውራውን አጠናክሮ ለማስቀጠልና የሽብርና ሌሎች በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በአግባቡ ለመከላከል ተጨማሪ ጥቆማዎችን መቀበል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷልም ነው ያለው፡፡

የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣ በውክልና፣ በአደራ፣ በጠባቂነት ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ ይዛችሁ የምትገኙ ሰዎች ይህ ማስታወቂያ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በሰባት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሪፖርት እንዲያቀርቡም ጠይቋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት፣ በራሳቸው በቤተሰቦቻቸውና በቅርብ ሰዎች ስም የያዙት በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኝ ንብረት አስመልክቶ ከሕዝቡ ተጨማሪ ጥቆማዎች በአካል፣ በስልክና በኢሜል እንዲቀርብ እየጠየቀ በአካል መቅረብ ለማይችሉ ጥቆማ አቅራቢዎች በሚከተሉት የስልክና ኢሜል አማራጮችን እንዲቀጠሙም ነው የጠየቀው፡፡

ስልክ ፡- +251112733154
Email: – assetrecovery@eag.gov.et

የሪፖርትና ጥቆማ ማቅረቢያ ቦታ ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሕንጻ 1ኛ ፎቅ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ሲሆን ሚቀርቡ ተጨባጭ ጥቆማዎች መንግስት ለጠቋሚዎች ማበረታቻ የሚሆን ተመጣጣኝ ክፍያ የሚፈጽም መሆኑን ተገልጿል፡፡

የህወሃት የሽብር ቡድን አባላት የሆኑ ንብረቶችን በኪራይ፣ በውክልና፣ በአደራ፣ በጠባቂነት ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ ይዘው ሪፖርት የማያደርጉ አካላት በሽብር አዋጁና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕጎች ተጠያቂ እንደሚሆኑ መግለጹንም የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.