Fana: At a Speed of Life!

በመቀሌ 84 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት ሠራተኛ ወደ ስራ ገበታው ለመመለስ ሪፖርት አድርጓል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በመቀሌ ከሚገኙት 2 ሺህ 26 የመንግሥት ሠራተኞች መካከል እስካሁን 84 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ ለመመለስ ሪፖርት ማድረጋቸውን የከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ ተናገሩ።

ከንቲባው አቶ አታኽልቲ ኃይለሥላሴ የመቀሌ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ የመቀሌ ከተማን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከነዋሪዎች ጋር በቅንጅት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የመደበኛ ፖሊስ አባላትም በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ሪፖርት እያደረጉ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በጎ-ፈቃደኛ እና መልካም ስነ-ምግባር ያላቸው ወጣቶች በከተማዋ ሰላምና መረጋጋት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በከተማዋ ከሚገኙ ሰባት ክፍለ ከተሞች መካከል በአምስቱ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡ አመራሮች መመደባቸውን ጠቅሰው፤ በቀሪ ሁለት ክፍለ ከተሞች ላይ ምደባ ለማካሄድ ህዝባዊ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለመንግሥት ሠራተኞች ባቀረበው ጥሪ መሠረትም  በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ 2 ሺህ 26 ሠራተኞች መካከል እስካሁን 84 በመቶው ወደ ሥራ ለመመለስ ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች በነበሩበት እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ተቀምጦ ጥሪ ቢደረግም ባለመምጣታቸው ምክር ቤቶቹ በህዝብ ምርጫ እንደ አዲስ እንዲቋቋሙ መደረጉንም ገልጸዋል።

ምክር ቤቶችና አመራር የተመደበላቸው ክፍለ ከተሞች ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ መግባታቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪ በከተማዋ  ተከስቶ የነበረው የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በፌዴራል መንግሥት እገዛ ችግሩ መፈታቱን አቶ አታኽልቲ ገልጸዋል።

የዋጋ ንረት ችግር እንዲፈታም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.