Fana: At a Speed of Life!

በመተንፈሻ መሳሪያዎችና ኦክስጅን እጥረት ሳቢያ ታካሚዎች አገልግሎቱን ሳያገኙ ለህልፈት እየተዳረጉ ነው – የኮቪድ19 ህክምና ማዕከላት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ህክምና ማዕከላት የሚገኙ የመተንፈሻ መሳሪያዎችና የኦክስጅን አቅርቦት አነስተኛ በመሆኑ በቫይረሱ ተይዘው ወደ ማዕከላቱ የሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎቱን ሳያገኙ ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑን የሚሊኒየም እና ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮቪድ19 ህክምና ማዕከላት ገልጸዋል፡፡

የሚሊኒየም ኮቪድ19 ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቫይረሱ ተይዘው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ላይ በማዕከሉ 210 የሚሆኑ ታካሚዎች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህ ውስጥም 27 የሚሆኑት በመተንፈሻ መሳሪያ እየታገዙ ሲሆን፣75 የሚደርሱት ደግሞ ኦክስጅን በመጠቀም ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ወደ ጽኑ ህክምና ከፍል የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎም ለታካሚዎች አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት አለመቻሉን ዶክተር ውለታው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም መሳሪያዎቹ ያለምንም እረፍት ለ24 ሰዓት እየሰሩ በመሆናቸው አቋማቸው እየወረደ መምጣቱን ነው የሚናገሩት፡፡

በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮቪድ19 ህክምና ማዕከል የፅኑ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ታሪኩ አሰፋ በበኩላቸው፣ ከባለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በቫይረሱ ተይዘው ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ አሁን ላይ  አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ማዕከሉ  የሚመጡ ጽኑ ታማሚዎችን ማስተናገድ አለመቻሉን ነው የሚገልጹት፡፡

ህክምናውን ለመጠባበቅ  ወረፋ ይዘው የተመለሱ ዜጎችን ተራቸው ሲደርስ ሲደወልላቸው ቤታቸው ሆነው ህይወታቸው ማለፉን መስማትም የተለመደ ሆኗል ይላሉ ዶክተር ታሪኩ፡፡

ከባለፈው መስከረም ወር ጋር ሲነፃጸር አሁን ላይ በማዕከሉ ውስጥ በቫይረሱ ሳቢያ ለህልፈት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር በ3 እጥፋ ማደጉን ዶክተር ውለታው ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ታካሚዎች መብዛት የህክምና ማዕከላትን ከማጨናነቁ ባለፈ በባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ስለሆነም ዜጎች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች በትክክል ገቢራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ከኮሮና ክትባት ጋር በተያያዘ ዜጎች አንዴ ተከትቤያለው በሚል የሚያሳዩትን መዘናጋት ማቆም እንዳለባቸው ዶክተር ታሪኩ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ዜጎች  ስለ ክትባቱ የሚወሩ አላስፈላጊ አሉባልታዎችን  ወደ ጎን በመተው ክትባቶችን ባገኙት አጋጣሚ መከተብ እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.