Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ለዘመናት የነበሩ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም በሚካሄዱ ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓቶች አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ በነበረው አለመረጋጋት የተፈጠረውን ቁርሾ በዘላቂነት ለመፍታት ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
በወረዳው ሚንጆ ቀበሌ ማዕከል ከ11 ቀበሌዎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች የነበረውን አብሮነት ለማስቀጠል ባህላዊ የእርቅ ስነ ስርዓት አካሂደዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ፥ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ወደ ልማትና ብልጽግና ለመግባት የሚካሄዱ የእርቅ ስነ ስርዓቶች በእውነት ላይ መመስረት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
እርቅ የፈጸሙ አካላትም÷ ወደ ሰላም ያልገቡ ቡድኖችና ግለሰቦች በጦርነት መጠፋፋትና ውድመት እንጅ ሌላ ውጤት አለመኖሩን ተገንዘብው በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የመንግስት ቀዳሚ አማራጭ ሰላም ማስፈን መሆኑን ጠቁመው÷ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ ባልሆነ አካል ላይ ግን የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላ ብለዋል፡፡
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው÷ በነበረው አለመረጋጋት የማንም ወገን ተጠቃሚ አለመሆኑን በመረዳት የአባቶችን የቆየ መልካም የግጭት አፈታት እሴቶችን በመጠቀም የጋራ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ወረዳው የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ በመሆኑ በተፈጠረው አለመረጋጋት ያጋጠመውን ችግር ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀም ቀጠናውን ወደ ሰላም በመመለስ ነዋሪዎች በመደበኛ ስራቸው ላይ እንዲሰማሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.