Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረንስና የእርቅ ስነ-ስርዓት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረንስና የእርቅ ስነ-ስርዓት ተካሄደ በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንስና የእርቅ ስነ-ስርዓት ተካሄደ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በተደረገው የሰላም ኮንፈረንስና እርቅ ላይ በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሀይል አመራሮች፣ የዞኑና የወረዳው አመራሮች እና ከ21 ቀበሌዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

የሰላም ኮንፈረንስና የእርቅ ስርዓቱ በአካባቢው ከ2011 ዓም ጀምሮ አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ ችግር እንዳይቀጥል የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች በአካባቢው ባህል መሰረት ቃለ መሃላ በመፈፀም እርቀ ሰላሙ ተከናወኗል።

በኮንፈረንሱ የተሳተፉ የወረዳው ነዋሪዎች የመርሃ ግብሩ መካሄድ እንዳስደሰታቸው ገልጸው÷ ባለፉት ሶስት አመታት በአካባቢው የተፈጠረው ችግር ‘በጁንታው ተላላኪ ሃይሎች የተፈፀመ ነው’ ሲሉ ተናግረዋል።

የአካባቢው ህዝብ ለዘመናት በልዩነት ውስጥ አንድነቱን ጠበቆ ሲኖር የነበረ ህዝብ መሆኑን ጠቁመው÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጁንታው ተላላኪ አመራሮች ይህን አንድነት ለመናድ ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

በአካባቢው የተፈጠረው ችግር በህዝቦች መካከል እንዳልሆነ ገልፀው አሁን ሰላም ሰፍኖ ወደ ጫካ እና ወደ አጎራባች አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ገልፀዋል።

የቀሩትም በቅርብ ጊዜ እንዲመለሱ እንደሚያደርጉ እና የፈረሱ ቤቶችን በጋራ እንደሚገነቡ ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

“ሁላችንም አንድ ኢትዮጵያዊ ነን” ያሉት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ከዚህ በኋላ ሰላማችን ዳግም ሊደፈርስ አይገባም ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ከግጭት የሚገኝ ትርፍ ስለሌለ ካለፈው ተምረን በቀጣይ ምንም ችግር እንዳይከሰት ተባብረን መስራት አለብን ብለዋል።

የማንዱራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ  ብመር አምሳያ÷ይህ የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረንስና እርቀ ሰላም በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው የወጡ ዜጎችን እንደገና መልሶ ለማቋቋምና መልሶ ለማደራጀት እንዲሁም ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት ቃለ መሃላ ለመግባት ነው ብለዋል።

ከእርቀ ሰላሙ በኋላ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማደራጀት እንደቀድሞ የወንድማማችነት ፍቅር መለገስ አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው÷ የሰላም ኮንፈረንስና እርቀ ሰላም መካሄዱ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

ማህበረሰቡ የህዝብን ሰላምና አንድነት የሚያደፈርሱ ፀረ ሰላም ሃይሎች ተደራጅቶ በማስወገድ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ አለበት ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዳንጉር ወረዳም እንዲሁ የሰላምና የእርቀሰላም ኮንፈረንስ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.