Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ በሚደርሰው ጭፍጨፋ የተሰማሩ የጥፋት ተዋንያኖችን በፍጥነት አድኖ ለሕግ የማቅረብ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመተከል ዞን በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሰው ጭፍጨፋ ሀገርን ለማፍረስ ከሚደረገው እኩይ ዓላማ የተለየ ባለመሆኑ በድርጊቱ የተሰማሩ የጥፋት ተዋንያኖችን በፍጥነት አድኖ ለሕግ የማቅረብ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራው ከፌዴራል እና ከክልል የተውጣጣ ከፍተኛ ልዑክ ዛሬ ወደ ስፍራው አቅንቷል።
በክልሉ ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እና ልዑኩ አስቀድሞ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን በተቀመጠው ዕቅድና አቅጣጫ አፈፃፀም ዙሪያ ግምገማ አካሂዷል።
አካባቢውን ለማረጋጋት አስቀድሞ የተቀመጠውን ዕቅድ እና አቅጣጫ ተፈፃሚ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ተደጋግሞ በዜጐች ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ ሊገታ በሚችል አግባብ እና የችግሩን አሳሳቢነት በሚመጥን መልኩ እንዳልተፈፀመ በግምገማው ተለይቷል።
በተለይ በቅርቡ በድባጤ እና ቡለን አካባቢዎች በዜጎች ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋና ማንነትን ዒላማ አድርጎ የደረሰው ጥፋት እጅግ አሳዛኝ እና በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አቶ ደመቀ ገልፀዋል።
ማንነትን ዒላማ አድርጎ ከአካባቢው የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለይቶ ለማስወጣት የሚደረገው ህገ-ወጥ እንቅሰቃሴ በፍጥነት ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ እርዳታ እንዲደርሳቸው እና ሁኔታውን ባገናዘበ መልኩ መልሶ የማቋቋም ስራዎች በፍጥነት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
በቀጣይ በአካባቢው ማህበረሰቡ ራሱን ለመከላከል እና ሰላሙን በዘላቂነት ለመገንባት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከፌዴራል እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት አካባቢውን ለማረጋጋት እና ዜጎችን ከጥፋት ለመታደግ ለተሰማሩ የፌዴራል እና የክልሉ ፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ ኮማንድ ፖስቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የችግሩን አሳሳቢነት የሚመጥን ስምሪት እና ዜጎችን ከጥቃት የመጠበቅ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.