Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ በርካቶች መደምሰሳቸውን ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ በርካቶች መደምሰሳቸውን በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል አስታወቀ።
በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉም ተገልጿል።
በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል አባል ብርጋዴል ጄነራል አለማየሁ ወልዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በመተከል ዞን በዜጎች ላይ ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ በርካቶች ሲደመሰሱ ከፊሎቹ ተማርከዋል።
ያመለጡ የታጣቂ ቡድኑን አባላት የማደን ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከሁለት ቀን በፊት በዞኑ የኦነግ ሸኔና የህወሃት ተላላኪ ታጣቂ ቡድን አባላት በፈጸሙት ጥቃት የ74 ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን ብርጋዴል ጄነራል አለማየሁ ገልጸዋል።
ግብረ ሃይሉ የታጣቂውን የሽፍታ ቡድን እንቅስቃሴ በመከታተል የተቀናጀ የህግ ማስከበር እርምጃ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ እና በዚህም በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን ጠቅሰዋል።
የታጣቂ ሃይሉን አባላት በማደን ተግባር የፀጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ጠንካራ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በንፁሃን ዜጎች ላይ በተፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ግብረ ሃይሉ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጾ፤ ግብረ ሃይሉ ይህንን እኩይ አላማ አንግቦ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን ሙሉ ለሙሉ በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ብርጋዴል ጄነራል አለማየሁ እንዳሉት ከትናንት ጀምሮ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል።
በዚህም ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ በአካባቢው ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አይፈቀድም።
ይህንን ገደብ ተላልፎ የሚገኝ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ካለ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ ታውቋል።
በታጣቂ ሃይሉ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ባልተገባ መንገድ የሚገልጹ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.