Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የልዩ ኃይልና የመደበኛ ፖሊስ አመራሮች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞንን ጸጥታ በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ በሁለተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ 460 የዞኑ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊስ አመራሮች ተመረቁ።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የዞኑ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮን ጨምሮ የመከላከያና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ የጸጥታ ኃይሉ የውስጥ አንድነቱን አጠናክሮ ለተልዕኮ መዘጋጀት እንዳለበት ገልጸዋል።

“በዞኑ የሚገኙ የመደበኛ ፖሊስም ይሁን የልዩ ኃይል፤ አመራርና አባል የማይናድ አንድነት ሲገነቡ የህዝቡም አንድነት ይጠነክራል” ያሉት ሌተናል ጄኔራል አስራት፤ የጸጥታ ኃይሉ በማንነትም ይሁን በብሔር አድሎ ማሳየት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

የጸጥታ ኃይሉ ከህዝብ በፊት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ከሁሉም በላይ መዘጋጀትና ሕዝባዊ አስተሳሰብ መገንባት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

የጸጥታ ሀይሉ አርዓያ በመሆንና በመልካም ስነ ምግባር መቆም እንዳለበት ሌተናል ጄነራል አስራት አሳስበዋል።

የምዕራብ ዕዝ የስልጠና ኃላፊ ኮሎኔል ሰይፈ ኤንጊ በበኩላቸው፤ የስልጠና ማዕከሉ በዞኑ ፓዌ፣ ቡለንና ጉባ ወረዳዎችን ማዕከል አድርጎ በሁለት ዙር ተሃድሶው መስጠቱን ጠቁመዋል።

ስልጠናው የጸጥታ ሀይሉ ህዝቡን በመልካም ስነ ምግባር በታማኝነት ማገለግል እንዲያስችል በማሰብ ወታደራዊ ባህልና ጨዋነት የህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆችና የጸጥታ ሀይል ደህንነት አጠባበቅ ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም 237 የጸረ ሽምቅ አድማ ብተና ወይም ልዩ ሀይል እና 222 መደበኛ ወይም ሕዝባዊ ፖሊሶች የአምስት ቀናት ሁለተኛ ዙር ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸረ ሽምቅ አድማ ብተና ፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ኢዶሳ ጎሹ የተሀድሶ ስልጠናው የጸጥታ ሀይሉ ያለበትን ክፍተት ለመፍታት እንደሚያስችል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.