Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በአመለካከት ላይ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በአመለካከት ላይ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ የአካባቢው ነዋሪዎች አሳሰቡ።

በፌዴራል መንግስት ተቋቁሞ የሕግ የበላይነት በማስከበር ላይ የሚገኘው ግብረ ኃይል ከመተከል ዞን ምሁራን ጋር ተወያይቷል።

በዞኑ ለተፈጠረው ችግር ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን ያነሱት ምሁራኑ በዋናነት ግን የወጣቱ አመለካከት በጥፋት ሃይሎች መመረዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ በማኅበራዊ ድረ ገፆች፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና በአመራሮች ሳይቀር አንድን ወገን የሚደግፉ፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩ መልዕክቶች አሁንም ድረስ እየተላለፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በነበረው ሁኔታ በተለያዩ አካላት የጥፋት መልዕክቶች ሲተላለፉና የማኅበረሰቡ አመለካከት ሲመረዝ ሃላፊነቱን የተወጣ አካል አለመኖሩንም አንስተዋል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በመተከል ዞን የሚኖሩና መላው ኢትዮጵያዊያን እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዞኑ አንድ ዜጋ ሲጎዳ በብሄሩ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ የሚያዝን ማኅበረሰብ ካልተፈጠረና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ የሚታገል ማኅበረሰብ ካልተፈጠረ ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚመዝንና በእኩል የሚያይ ዜጋ የመፍጠር ጉዳይ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በተለይ መገናኛ ብዙሃን፣ የሠብዓዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾች እንዲሁም ሌሎች ገለልተኛ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ሲገባቸው “ዘንግተውታል” ነው ያሉት ምሁራኑ።

በተለይ የመተከልን ሠላም ማጣት በተመለከተ አንዳንድ የማኅበራዊ አንቂዎች፣ ሃላፊነት የጎደላቸው አመራሮችና መገናኛ ብዙሃን ወገንተኛና አድሏዊ የሆኑ ችግሩን የሚያባብሱ መመረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አመላካችና ሚዛናዊ ስራ ነው የሚያስፈልገው ነው ያሉት ምሁራኑ መንግስት ከዚህ የወጡ አካሄዶችን እያየ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

ውይይቱን የመሩት የኮማንድ ፖስቱን የፀጥታ ሃይል በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ችግሩ ሆን ተብሎና ለ30 ዓመታት ታስቦበት የተሰራ መሆኑን ግብረ ሃይሉ ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር ባካሄዳቸው ውይይቶች መገንዘቡን ተናግረዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.