Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በመንገድ ትራፊክ አደጋ በቀን የ13 ሰዎች ህይወት ያልፋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ መንገድ ደህንነት አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የተዘጋጀውን የዳሰሳ ጥናት መሠረት ያደረገ ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የመንገድ ደህንነት ዳሰሳ ጥናቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የልማት ኮሚሽን አስተባበሪነት የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።

በዳሰሳ ጥናቱ በሀገሪቱ በሚከሰት የመንገድ ትራፊክ አደጋ በቀን የ13 ሰዎች ህይወት የሚያልፍ መሆኑ ነው የተመላከተው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአስፓልት መንገድ ሽፋን 14 በመቶ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፥ 80 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚደርሰው በአስፓልት መንገድ ላይ መሆንም አመላክቷለል።

በሀገሪቱ ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚከሰት መሆኑ ተገልጿል።

ለዚህም የአሽከርካሪዎችና መንገደኛች ግንዛቤ ማነስ፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ደካማ መሆን፣ ያረጁ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መበራከት፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ክፍተት፣ የቁጥጥር ስርዓቱ ደካማ መሆን፣ የመንገድ ዲዛይንና ጥራት የችግሩ መንስኤዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚከሰትን ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የመንገድ ደህንነትን አስቀድሞ በመረዳትና ለጉዳቱ አሳሳቢነት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በማካሄድ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ የሚቀርበው የዳሰሳ ጥናቱ ውጤትም ሚኒስቴሩ በዘርፉ እያከናወነ ላለው ስራ አስፈላጊ ግብዓቶችን እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል።

በቀጣይ የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የመንገድ ደህንነት አደጋ ለመቀነስ ከህብረተሰቡ ጋር በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.