Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሐሰተኛ ገንዘብ ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብና በገንዘቡ ሲገለገሉ የነበሩ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሐሰተኛ ገንዘብ ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ እና በሐሰተኛው ገንዘብ ሲገለገሉ የነበሩ ስድስት ተጠርጣሪዎች ከእነ ማስረጃው ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ሐሰተኛ ገንዘብ ሲያዘጋጅ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው በሐሰተኛው ገንዘብ ሲገለገሉ ተይዘው ምርመራ በተደረገባቸው አራት ተማሪዎች መነሻነት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የላንቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ስለሺ ሸንቁጤ እንደገለፁት÷ ተማሪዎቹ ሐሰተኛ ባለ 200 የብር ኖት ይዘው በሚማሩበት ትምህርት ቤት መዝናኛ ክበብ ግብይት ለመፈፀም ሲሞክሩ የክበቡ ባለቤት ተጠራጥረው ጉዳዩን ለፖሊስ በማሳወቃቸው ተማሪዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ የማጣራት ስራ ተሰርቷል።

በተማሪዎቹ ላይ በተደረገው ምርመራ ሐሰተኛ ገንዘቡን ከሚያዘጋጀው ግለሰብ በህጋዊ 500 ብር ሐሰተኛ 1 ሺህ 500 ብር እንደሚቀይሩ መረጋገጡን ነው የገለጹት፡፡

ከትናንት በስቲያ በክፍለ ከተማው ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ካዛንቺስ አፍሪካ ዳቦ ቤት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የተጠርጣሪው ቤት በሕግ አግባብ በተደረገ ፍተሻ 13 ሺህ 200 ሐሰተኛ ብር እና ብሩን ለማዘጋጀት የሚጠቀምባቸው የተለያዩ ቁሳቁስ በማስረጃነት መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከአራቱ ተማሪዎች በተጨማሪ ሐሰተኛ ገንዘቡን ሲያዘጋጅ የነበረው ግለሰብ እና በግብረ አበርነት የተሳተፉ 2 ተጠርጣሪዎች በአጠቃላይ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የምርመራው ሂደት መቀጠሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.