Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሕዝባዊ ሰራዊቱ የሚመራበት አዲስ ደንብና ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕዝባዊ ሰራዊት የሚመራበት አዲስ ደንብና ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሰላም እሴት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በሰጡት ማብራሪያ÷ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ከ246 ሺህ በላይ የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ከፖሊስ ጋር በቅንጅት ለመሥራት በሚያስችል መልክ ከጓድ እስከ ብርጌድ ፖሊሳዊ አደረጃጀትን በተከተለ መንገድ የሪፎርም ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

ከሕልውና ዘመቻው ወቅት አንስቶ የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት የከተማችንን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥና የሽብር ቡድኖችን አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመግታት ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እስከ መስዋዕትነት የደረሰ ዋጋ መክፈላቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕገ ወጥ ጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ ለሽብር ተግባር የተዘጋጁ የክልል ፖሊስ የደንብ ልብሶችን መያዝ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ለእኩይ ዓላማ የተከማቹ የልዩ ልዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች፣ ለሽብር እንቅስቃሴ የተዘጋጁ ሀሰተኛ መታወቂያዎችን ጨምሮ በርካታ የተደራጁ ወንጀለኞችንና የሽብር ድርጊቶችን ሕዝባዊ ኃይሉ ከጸጥታ ተቋማት ጋር በጋራ ሲከላከል መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

የፖሊሳዊ አደረጃጀት ሪፎርሙ ያስፈለገው÷ አገልግሎቱን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ፖሊስ ከሕዝባዊ ሠራዊቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ ባለው ስራ÷ የመኪና ስርቆት፣ የተደራጀ ዘረፋና መሠል ደረቅ ወንጀሎች 50 ከመቶ መቀነሳቸውንም ወ/ሮ ሊዲያበማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡

አዲስ የተዘጋጀው የሕዝባዊ ሠራዊት ረቂቅ ደንብና መመሪያ ትዕዛዝ ከበላይ የሚወርድበት የራሱ የዕዝ ሰንሰለት እንዲኖረው ተደርጎ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

በአዲሱ የሕዝባዊ ሠራዊት ረቂቅ ደንብና መመሪያ መሠረት የሠራዊቱ አባላት ማንነታቸውን የሚገልጽ የደንብ ልብስና ኃላፊነታቸውን በዝርዝር የሚገልጽ የመታወቂያ ካርድ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.