Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በህገ ወጥ መልኩ የተከማቸ መድሃኒት ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ ሁለት ክፍለ ከተሞች በሕገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ መድሃኒት በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ፤ ባለፈው አንድ ወር ከፌዴራል ፖሊስና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በመዲናዋ በሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ላይ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተደረገው ጥናት ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር አለባቸው የተባሉ ስድስት ቦታዎች መለየታቸውን አስታውሰው በአራቱ ላይ ፍተሻ ተካሂዷል ነው ያሉት።
በዚህም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 “ፓስተር አደባባይ” አካባቢ እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት “አራት መንታ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ብዛት ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ተከማችተው መያዛቸውን ጠቁመዋል።
በህገ ወጥ መልኩ ተከማችቶ የተገኘው መዲሃኒት በአዲስ ከተማ በግለሰብ በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ በአንድ መድኃኒት አከፋፋይ ድርጅት የጥበቃ ቤት ውስጥ ነው።
መድኃኒቱንና የህክምና ግብአቶቹን አከማችተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ከተያዙት መድኃኒቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡና በጥንቃቄ ተከማችተው መከፋፈል ያለባቸው እንዲሁም በጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ብቻ የሚታዘዙ እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።
ለህጻናትና ለእናቶች የሚሰጡ መድኃኒቶችና ከመንግስት የጤና ተቋማት የተሰረቁ የሳንባ ነቀርሳና የኤች አይቪ ኤድስ መመርመሪያ ኪቶችም መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜ የተያዙት መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶች በአጠቃላይ የሚያወጡት ወጪና ብዛታቸው ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሕብረተሰቡ የጤና ግብአቶች ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው ተቋማት ብቻ መግዛት እንዳለበትና በህክምና ባለሙያ መታዘዝ ያለበትን ከባለሙያ ትዕዛዝ ውጭ መጠቀም እንደሌለበት ገልጸው ሕብረተሰቡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ በ84 82 የነጻ የስልክ መስመር ማሳወቅ እንደሚችልም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.