Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 34 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 34 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የተገኙት ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በጦር መሳሪያ በመታገዝ ትላልቅ ተቋማትንና ድርጅቶችን ሲዘርፉና የድብደባ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተደራጀ መንገድ በዘረፋ ተግባር የተሰማሩት ተጠርጣሪዎቹ ውድ እቃዎችና ገንዘብ ያለበትን የሚያጠና፣ ጊዜና ቦታ አመቻችቶ የሚዘርፍና የዘረፈውን የሚሸጥ ሶስት ቡድን እንዳላቸው ደርሰንበታል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ከተማዋ የደህንነት ስጋት እንዳለባት በማስመሰል የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ይህን ተላልፈው ከተገኙ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለንም ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ የሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ ከ4 ሺህ 180 በላይ አዲስ ምልምል ፖሊሶች ኮሚሽኑን መቀላቀላቸውን በመግለፅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ነው የጠቀሱት፡፡

በመዲናዋ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ማጭበርበር ወንጀሎች መሰማራታቸውን ደርሰንበታል ያሉት ኮሚሽነር ጌቱ ለፍርድ ቀርበው በማረሚያ ቤት የሚገኙ መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

በቀጣይም በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት እንዳይሳተፉ ለመከላከል በሚያርፉባቸው ሆቴሎችና እንቅስቃሴ በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች የፖሊስ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የኅብረተሰቡ መዘናጋት ‘አሳስቦኛል’ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን በማይተገብሩ ግለሰቦች ላይም እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.