Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሽመልስ እሸቱ፥ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ እድሳት ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በዘመናዊ እና ለስራ ምቹ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በህንፃው ውስጥ የሚገኘው ባህልና ቴአትር አዳራሽን ጨምሮ አጠቃላይ የህንፃው እድሳት ክንውን 71 በመቶ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ያለው የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት የአድዋን ታሪክ ለመዘከር በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ሲሆን፥ በውስጡ የአድዋ ሙዚየም ፣ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት እና የታሪክ ልህቀት ማዕከል እንደተካተቱበትም ነው የተናገሩት።

የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከ60 በመቶ በላይ መድረሱንና በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ወራት አካባቢ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናልም ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም 19 ሺህ ካሬሜትር ስፋት ያለው የቤተ መጽሐፍት ግንባታ 93 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፥ ለህንፃው ግንባታ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ተበጅቶለት እየተገነባ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም ከ5 ሺህ እስከ 7 ሺህ የዲጂታል ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት መስጠት ያስችላል ማለታቸውን ከከተማው ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሆኖ እየተሰራ ሲሆን፥ በአንድ ጊዜ 1 ሺህ 400 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ተሽከርካሪ ማቆሚያና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት በሚያስችል መልኩ ግንባታው ተጠናቆ በቅርብ ቀን አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የቤተ መንግስት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ ክንውኑ 79 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ ለ1 ሺህ ተሽከርካሪዎች የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.